ጾመ ሐዋርያት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

‘‘ጾም’’ በፊደላዊ ትርጕሙ ‘ጾመ’ ተወ፣ ታቀበ፣ ታረመ፣ ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ነው፤ የቃሉም ፍቺ ምግብን መተው፣ መከልከል፣ መጠበቅ ማለት ነው፤ ስለዚኸም ጾም ለክፉ ሥራ ከሚያነሣሱ የምግብ ዓይነቶች፣ በቤተ ክርስቲያን የሥርዐት መጻሕፍት ከተወሰነው ጊዜ ሳያጓድሉ፣ መከልከል፤ ወይም ለተወሰነ ጊዜ እና ሰዓት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ኹሉ መወሰን (መታቀብ) ማለት ነው፤ ለሰውነት የሚያምረውን እና የሚያስጎመዠውን ነገር ኹሉ፣ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ብሎ መተውም ነው፡፡

በሌላም በኩል ጾም ማለት ጥሉላት መባልዕትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከመብል እና ከመጠጥ ከሌላውም ክፉ ነገር ኹሉ መጠበቅ፤ መግዛት፤ መቆጣጠር፤ በንስሓ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እና ርሱንም ደጅ መጥናት፤ ‘ማረኝ፤ ይቅር ’ በለኝ በማለት፣ እግዚአብሔር ፊት በመንበርከክ፣ የርሱን ምሕረትን ለመቀበል መዘጋጀት ማለት ነው፡፡

የጾም ጥቅሙ እና አገልግሎቱ በጥንት ከአበው ጀምሮ በጎላ በተረዳ ነገር የታወቀ በመኾኑ፣ መጾማችን ፈቃደ ሥጋን ለነባቢት ነፍስ ለማስገዛት ይጠቅማል፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን ለመለመን እና ከርሱም መልካም የሆነውን ኹሉ ለመቀበል ይጠቅማል፡፡

አኹን ያለንበት ወቅት፣ ጾመ ሐዋርያት ተብሎ ይጠራል፤ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከተቀበሉ በኋላ፣ ለስብከተ ወንጌል ከመሠማራታቸው በፊት፣ የጾሙት ጾም ነው፤ ይኸውም በዓለ ሃምሳ ወይም በዓለ ጰራቅሊጦስ በዋለ በማግስቱ ሰኞ ይጀመርና፣ ፋሲካው (መፍቻው) ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ ባረፉበት በሐምሌ አምስት ቀን ነው፤ የጾሙ ቀናት ቊጥሩ ከ፲፭ እስከ ፵፱ ቀናት ከፍ እና ዝቅ ይላል፤ በሰኔ ወር ስለ ሚጾምም ስለኾነ፣ የሰኔ ጾም ተብሎ ይጠራል፤

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው እኛ ፈሪሳውያን እንጾማለን፤ ያንተ ደቀ መዛሙርት ግን አይጾሙም፤ ለምንድን ነው ብለው በጠየቁት ጊዜ፣ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፣ እኔ አብሬአቸው ስላለኁ፣ ሚዜዎች አይጾሙም፤ እኔ ከእነርሱ የምለይበት ጊዜ ይምጣልና፣ ያን ጊዜ ይጾማሉ በማለት የርሱ ደቀ መዛሙርቱ (ሐዋርያት) ይኸነን ጾም እንደሚጾሙት ተናግሮ ነበር፤ ሐዋርያትም፣ ይኸነን የጌታችንን ቃል መሠረት አድርገው ጾመው፣ ፈተናውን ኹሉ ድል ነሥተውበታል፡፡

ምንም እንኳን ሐዋርያቱ የጾሙት ጾም ቢኾንም፣ ዛሬም በረከት ለማግኘት የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለን፣ በየዓመቱ እንደ ዐዲስ ደስ ብሎን፣ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለፍርድ መጥቶ፣ መንግሥቱን ከሚያወርሳቸው ቅዱሳኑ ጋር እንዲደምረን፣ የነቢያት እና የሐዋርያት፣ የጻድቃን እና የሰማዕታት አምላክ ተለመነን እያልን እንማጸንበታልን፤ እንጾመዋለን፡፡

ይኽነን ጾም፣ ከሌሎች አጽዋም ጋር አንድ አድርጎ ኹሉም ሊጾመው እንዲገባ የታወጀ ቢኾንም፣ ብዙ ሰዎች አይጾሙትም፤ ምን አልባትም ሐዋርያት የጾሙት ጾም ስለ ኾነ ይመስላል፣ ሊጾሙ የሚፈልጉትንም ሰዎች የቄስ ጾም ስለ ኾነ፣ እናንተን አይመለከታችኁም በማለት፣ ሲያከላክሉ እና የሚጾሙትንም ሲነቅፉ የሚደመጡ ሰዎች አሉ፤ ይኽም ተሳስቶ ማሳሳት፣ ደክሞ ማድከም ነው፤ ጾምን መሻር፣ መብልን ወዶ፣ ስስትን ማጉላት ነውና፡፡

 

ጾም ከምን ከምን

ጾሙን ፍጹም ለማድረግ ከምን ከምን መጾም እንደሚገባን ጥቂቱን እንመልከት

 1. ከጥሉላት መባልዕት
 • በጾም ወራት የእንስሳት ተዋጽኦ የኾኑት ሥጋ፣ ወተት፣ ዕንቁላል፣ ዐይብ… መመገብ አይፈቀድም፤ ቅባትነት ካላቸው እና ሥጋን ከሚያፋፉ መባልዕት (ምግቦች) መከልከላችንም ለከንቱ ሳይሆን፣ ሥጋዊ ጉልበትን በማድከም መንፈስን ለማበረታታት ነው፤ ክቡር ዳዊት ‘‘ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፣ ሥጋዬም በማጣት ከሳ’’ያለው ይኽን ሲልጽ ነው፡፡ (መዝ.፻፰፥፳፬/108፥24)
 • ከዚኽም በላይ በጾም ወቅት መጥኖ መመገብም እንዲገባ ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምራለች፤   ምክንያቱም ሰው እንዳገኘ የሚበላ እና የሚጠጣ ከኾነ፣ የእንስሳት ባሕርይ ትሰለጥንበታለች፤ እንስሳዊ ግብርም ታስፈጽመዋለች፤ መብል መጠጥ ልቡናን ያደነድናልና፡፡

 

 

 1. ከሚያሰክር መጠጥ
 • በተቀደሱ አጽዋም ክርስቲያን የኾነ ኹሉ፣ ከሚያሰክር መጠጥ መለየት ሃይማኖታዊ ግዴታው ነው፤ አትጠጡ በመባሉም፣ ብዙ ጠጥተው እንዳይሰክሩ እና ሌላውንም ኀጢአት እንዳይሠሩ ነው፤ ነቢዩ ዳንኤል ይኸነን ሲያጠይቅ ‘‘ጠጅም በአፌ አልገባም’’ ብሏልና፤ መጠጥ ማዝወተርም ለኃጢአት መሠረት መገኛ ነው፤ ይኽ ማለት ግን የጾሙ ወራት ከተፈጸመ በኋላ፣ ሰው እንደ ፈለገ አብዝቶ መጠጣት መስከር አለበት ማለት አይደለም፡፡

 

 1. ከሩካቤ መከልከል
 • ይኽ በተቀደሰ ጋብቻ ተወስነው በሕግ ጸንተው የሚመላሰሉ ክርስቲያን ኹሉ የሚመለከት  ነው፤ ከጋብቻ ውጪ ላሉት አይከለሉም ማለት ሳይኾን፣ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ፍትወት ቀስቃሽ ነገሮችን መፈጸም፣ አስቀድሞም ቢኾን (ከአጽዋት ውጪም ቢኾን) አልተፈቀደምና ነው፡፡  
 • ስለዚህ በተቀደሱ ወርኃ አጽዋም በጋብቻ ያሉትም ቢኾን፣ ባል በአንድ አልጋ፣ ሚስት በሌላ አልጋ፣ ወይም ባል ከመጋረጃ ውጪ፣ ርሷ ከመጋረጃ በውስጥ ሊተኙይገባቸዋል ማለት ነው፡፡
 • ይኽን ትእዛዝ ጥሶ የሥጋን ፍላጎት ማስተናገድ፣ ኹለት ነገሮችን ያመለክተናል፤ ለሥጋ ፍላጎት የምንገዛ እና ለነፍስ ፍላጎታችንን ከመፈጸም ቸል ያልን መኾናችንን፤ ዳግመኛም የእግዚአብሔር ፍቅር የጎደለብን እና የምንሠራውን ሥራ ኹሉ ለእግዚአብሔር ብለን የማንሠራ መኾናችንን ያመለክታል፤ ምክንያቱም የጾም ዓላማ ከሥጋ ይልቅ፣ ለእግዚአብሔር መገዛትን መግለጽ ነውና፡፡

 

 

 1. የሰውነታችን ሕዋሳትን ከክፉ ተግባራት መጠበቅ
 • ጾም ለሆድ ብቻ የሚታወጅ ሕግ አይደለምና፣ መላ ሕዋሳትም ጭምር የሚያጠቃልል በመኾኑ፣ ዕለት ተዕለትም የማይቋረጥ ጾም (ዐቂበ ሕዋሳት) ልንጾም ክርስትናችን ያስገድደናል፤ ይኽም ቅዱስ ያሬድ በድጓው ኹሉን አንድ አድርጎ ‘‘ዐይን ይጹም፣ እምርእየ ሕሡም፣ ዕዝን ይጹም፣ እምሰሚዐ ሕሡም፣ ልሳንኒ ይጹም፣ እምተናግሮ ሕሡም፣ በተፋቅሮ’’ ይላል፤ ሊቁ በዐይን፣ አንደበት እና ዦሮ መነሻነት፣ መላ ሕዋሶቻችንን በፍቅር ኾነው መጾም እንዳለብን ገልጾልናል፡፡
 • በጾም ወራት መላ የሰውነታችን ሕዋሳት ከክፉ ተግባራት መጠበቅ፣ እርም ከኾነው ነገር ኹሉ መራቅ ካልቻሉ፣ ጾማችን በረከት ለማሰጠት፣ ግዳጅ ለመፈጸም ዐቅም የላትም፤ መንፈሳዊ ሰው በእጁ ይመጸውትበታል፣ በእግሩ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ይሔድበታል፤ በጆሮው ስብሐተ እግዚአብሔር ይሰማበታል፤ በዐይኑ ምስጢር ይመለከትበታል፤ በልቡ በጎ ያሰብበታል፤ በአንደበቱ በጎ ይናገርበታል፤ በፍጻሜ ዘመኑ በሰማዕትነት ይሞታል፡፡
 • ክርስቲያን በጾም ወቅት ሊከለከሉ የሚገባቸው ብቻ ሳይኾን፣ ሊይዟቸው፣ ሊተገብሩዋቸው የሚገቡ መልካም ነገሮች አሉ፤ እነዚህም ንስሓጸሎትራስን ማዋረድ (ትሕትና)ፍቅርገለልተኛነት፣ ጸጥተኝነት (አርምሞ)ራስን መግዛት (መቆጣጠር)ስግደትልግሥናቅዱሳት መጻሕፍትን መመልከትምስጋና እና ክብርን ከመውደድ መውጣትን መለማመድፈሪሃ እግዚአብሔር ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡

በመጨረሻ ማንኛውም ጸዋሚ (ጿሚ) በሕሊናው ቢያንስ ኾለቱን ጉዳዮች ሊያስታውሳቸው ይገባል፤

፩. ጾሙን የተቀደሰ ማድረግ፡-

 • ጾምን የተቀደሰ ማድረግ ማለት፣ የጾም ቀናትን ለእግዚአብሔር መቀደስ፣ መለየት ማለት ነው፤ የጾም ዕለታት ለእግዚአብሔር ብቻ ይውላሉ እንጂ፣ ዓለማዊ ሥራዎች አይሠራባቸውም፤ ይኽም በነቢዩ ኢዩኤል ‘‘ጾምን ቀድሱ’’ ተብሎ የተነገረው ነው፡፡
 • ምክንያቱም የተቀደሰ ጉባዔ፣ ጾምንለእግዚአብሔር ለመቀደስ የተስማማ ነውና፤ በርግጥ፣ በዓለም ያለ ሰው፣ ዕለት ተዕለት ወደ የሥራው ስለሚሠማራ፣ ሙሉ ጊዜውን ለእግዚአብሔር ማዋል ባይጠበቅበትም፣ ቢያንስ ጾሙን ለመቀደስ ጊዜውን መሠዋት ይገባዋል፡፡

 

፪.  መንፈሳዊ ዓለማ እና ይዘቱን መገንዘብ፣

 • ክርስትና በዓላማ የሚጓዙበት እንጂ፣ በልማድ የሚኖሩት ኑሮ አይደለም፤ዓላማን ሳይረዱ መንገድ መጀመር፣ መድረሻው ስለማይታወቅ በጉዞው አቅጣጫን መሳት፣ መውደቅ እና መንገድ መቅረትን ያስከትላል፤ ‘‘በምትሔድበትም ኹሉ እንዲከናወንልህ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል’’ እንደ ተባለ፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳንዝል፣ ዓላማችንን መረዳት እና በተስፋ መጓዝ ይገባናል፡፡    (ኢያ ፩፥፯-፱/1፥7-9)

 

 • የጾም ዓላማ፣ ፍቅረ እግዚአብሔር ነው፤ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር የተነሣ፣ ነፍሳችን ከርሱ ጋር ኅብረት እንዲኖራት ስለ ምንሻ፣ እንጾማለን፤  ሥጋችን የነፍሳችንን መንገድ አጨናንቆ እንዳይይዘው እና እንዳይጎትተው፣ ጾም አስፈላጊ ነው፤ በእግዚአብሔር ፍቅር መደሰት በሕይወታችን ሙሉ ልንይዘው የሚገባ ጠባይ መሆን ይኖርበታል፡፡

 

ሐዋርያት ጾመው፣ ድል ያደረጉትን ዓለም፣

 እኛም የምናሸንፍበትን ኀይል እንዲሰጠን፣

እምላከ ሐዋርያት ይለመነን፤

አሜን፡፡

ትርጉም »