★ “ሕማማት” መግቢያ የተወሰደ ★
…. ‹ሕማማት› በተሰኘው በዚህ መጽሐፍ ላይ ስለ አዳም ውድቀትና ስለ አምላክ ሰው መሆን ምክንያት የመሳሰሉትን እጅግ ሰፋፊ ርእሶች ሳንነካ ከሐሙስ ማታ እስከ ዓርብ ዓሥራ አንድ ሰዓት ያለውን የጌታችንን የሃያ ሰዓታት ሕማማት እንዳስሳለን፡፡ ብቻውን መጽሐፍ የሚወጣውን የጌታችንን የመጨረሻውን ራትና የምሥጢረ ቁርባንን ምሥረታ ሳንነካ ጌታችን ከተያዘበት ከጌቴሴማኒ አትክልት ሥፍራ እንጀምራለን፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ለጌታችን መያዝ ተባባሪ የነበረውንና የጌታችን የሕሊና ቍስሉ ከነበረው ከአስቆሮቱ ይሁዳ እንጀምራለን፡፡ ከዚያም በሁለተኛው ምዕራፍ ጌታችን ተይዞ እስከ ጠዋት ድረስ ሲፈረድበትና ሲንገላታ ወዳሳለፈበት የሊቀ ካህናቱ ጊቢ አብረን ገብተን እናድራለን፡፡ ሲነጋም ወደ ጲላጦስ አደባባይ ሔደን የፍርዱን ሒደት እንከታተላለን ፤ ወደ ሔሮድስ ሲወስዱት እንከተለዋለን፡፡
ሲገርፉት ቆመን እናያለን ፣ይሰቀል ሲሉም እንሰማለን፡፡ ከዚያም ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ መስቀሉን ይዞ ሲሔድ በእግረ ሕሊናችን እንከተለዋለን ፣ ከስምዖን ጋር እናግዘዋለን ፣ ከገሊላ ሴቶች ጋር አብረን እናለቅሳለን ፣ ከመስቀሉ ሥር ከእናቱና ከዮሐንስ አጠገብ ቆመን በመስቀል ላይ ሆኖ የሚናገረውን ከታች ሆነን እንሰማለን፡፡ በመጨረሻም ነፍሱ ከሥጋው መለየቱን አይተን ፣ ከለንጊኖስ ጋር በጎኑ ውኃ ተጠምቀን ፣ ከኒቆዲሞስና ከዮሴፍ ጋር አልቅሰን እንቀብረዋለን ፤ ስለ መዳናችን እየተደሰትን ስለ መከራው እናለቅሳለን፡፡ ትንሣኤውን ተስፋ አድርገንም ‹ሕማማት› የተሰኘውን መጽሐፍ ንባባችንን እናበቃለን፡፡
‹የሕማማቱ› ታሪክ የሰው ልጅ ድኅነት የተፈጸመበት የትልቅ ፍቅር ፣ የይቅርታና የምሕረት ታሪክ ነው፡፡ አንድ ሊቅ እንዳለው ‹‹በእያንዳንዳችን ውስጥ እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚሞላው አንዳች ባዶነት አለ›› መከራውን ማንበባችንም ይህንን ባዶነታችንን ለመሙላትና በንስሓ ለመመለስ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዓላማም በምናነባቸው የሃያ ሰዓታት የወንጌሉ ክስተቶች መነጽርነት ራሳችንን ፈልገን እንድናገኝ መርዳት ነው፡፡ የኦርቶዶክሳዊው የመጽሐፍ ቅዱስ አነባበብ ስልት አንዱ መገለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ራስን ፈልጎ ማግኘት ነው፡፡
ከበረሃ መነኮሳት አባቶች አንዱን ‹ክርስቶስ በጎችና ፍየሎችን በግራና ቀኝ አቆማለሁ ያለው ስለ እነማን ነው?› ብለው ቢጠይቁት ‹‹በጎቹን እርሱ ያውቃቸዋል ፤ ከፍየሎቹ ግን አንዱ እኔ ነኝ›› ብሎ መልሶ ነበር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማችን ተቀይሮ እንጂ የሁላችንም ታሪክ ተጽፎአል፡፡ በወንጌሉ ቀድሞ ከተጻፈው ታሪክ እንድንማርና ታሪካችንን እንድንለውጥ ‹ለትምህርታችን› ተጽፎአል፡፡ (ሮሜ ፲፭፥፬)
ወዳጄ ሆይ ፤ እባክህን ጌታችን ከተያዘበት ሐሙስ ማታ እስከ ተቀበረበት ዓርብ ያለው ክስተት ውስጥ ራስህን ፈልገው፡፡ በዚያ ከነበሩት ሰዎች አንተ ማንን ትመስላለህ? ወዳጅ መስሎ እየሳመ የሚሸጠው ይሁዳ አንተ ነህ? ወይንስ ፈርቶ የሚክደውን ጴጥሮስ? በእርግጥ አንተ ማንን ትመስላለህ? የአንተ ጠባይ በእነዚያ ሃያ ሰዓታት ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ማንን ይመስላል?
ጌታን አስረው እያዳፉ የወሰዱትን ትመስላለህ? ወይንስ አንተ ማን ነህ? በሐሰት የሚሰክሩበት ውስጥ ነህ? ወይንስ ያለ ጥፋቱ አስረው ከሚያንገላቱት ውስጥ ነህ? ያለ ሕግ አግባብ በግፍ ከፈረዱበት ውስጥ ነህ? ወይንስ ገዢዎችን ለማስደሰት ብለው በጥፊ ከሚማቱት ውስጥ ነህ? እንደ ጲላጦስ ዓይነት ዳኛ ትሆን? ንጹሕ መሆኑን እያወቅህ ገርፈኸው ይሆን? ከሆነ ‹ንጹሕ ነኝ› ብለህ ብትታጠብም አጥፍተሃል፡፡ ይሰቀል ሲባል አብረው ከሚጮኹት ውስጥ ነህ? ከሔሮድስ ጭፍሮች ጋር ስቀህበታል ወይንስ ከገሊላ ሴቶች ጋር አልቅሰህለታል? ወዳጄ ሆይ በዕለተ ዓርብ ከነበሩት አንተ ማንን ትመስላለህ? የቀኙ ወንበዴ ነህ ወይንስ የግራው ፣ የቆምከው ከሰደቡት ጋር ነው ወይንስ ከእናቱ ጋር?
የምታውቃቸውን የሌሎች ሰዎችን ጠባይ ለማመሳሰልና ‹ይኼማ እገሌን ለመንካት ነው› እያልክ ከመንፈሳዊ መጽሐፍ ውስጥ ሥጋዊ ቅኔ ለማውጣት አትሞክር ፣ እባክህ ራስህን ብቻ ፈልገው ፤ የእግዚአብሔር ቃል መስታወት ነው ፤ በመስታወት ደግሞ የራስ እንጂ የሌላ ሰው ፊት አይታይም፡፡ (ያዕ. ፩፥፳፫)
ሕማማት ገጽ 23

ትርጉም »