• የሰንበት ትምህርት ቤት አመጣጥ ታሪክ

የሰንበት ትምህርት ቤት የሚለውቃል Sunday school ከሚለው እንግሊዝኛ ቃል የተወሰደ ይመስላል፡፡ ይህም ኢንግሊዛዊው የአንጌሊካን ወንጌላዊ ሮበርት ሬይክስ (፲፯፻፷፭ዎች-፲፰፻፲፩) ቲሞቲ ላርሰን በኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት የጀመረውን የሠራተኛው መደብ ቤተሰቦችና ድኾችን ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ለማስቻል በሚል በ፲፯፻፹ዎቹ በሰንበት ቀን ትምህርት ያስተምር የነበረውን በማሰፋፋትና በማሰተዋወቅ ለሃይማኖት ትምህርት በማዋል እንደጀመረው ና በስፋት እንዳስተዋወቀው ታውቋል፡፡(christianitytoday.com)

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን የዚህ ጥናት አቅራቢ እሰከሚያውቀው ድረስ የተጠና ጥናት ባያገኝምበማኅበር ስም በመሰባሰብ የሰንበት ትምህርት ቤት ቅርጽ ያላቸው ማህበራት የ፲፱፻፴፪ ቱን የጠላት ወረራና ድል መሆኑን ተከተሎ እንደተመሰረቱ የሚገልጹ ጽሁፎች አሉ፡፡ ማኅበር የሚለውቃል ደስታ ተክለወልድ በመዝገበ ቃላት መፍቻቸው ማኅበር (ራን) በቁሙ አንድነት ጉባዔ ሸንጎ ብዙ ሰው ቤተ ክርስትያን፡፡ ሥርዓተ ማኅበር ዕቀብ ማኅበርነ ማኅበሮሙ ለነቢያት ማኅበረ ሕዝብ፡፡ ማኅበረ ሠለስቱ አስማት ብለው ተርጉመውታል፡፡

ተክለ ሃይማኖት የተባለ የቤተክርስትያን ጋዜጣ ዜና መዋዕል በመሰከረም ፳፪ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ.ም የተማሪዎች ኅብረት የሚል ማኅበር በ፲፱፻፴፯ ዓ.ም እንደተጀመረ ገልጾ ጽፏል፡፡ ይኸውም ማኅበር በግብፃዊው መምህር ሰዐድ የእሁድ ትምህርት እንቅስቃሴን ሲመሠርቱ የት/ቤቱ ዳይሬክተር የነበሩት ቄስ ሀብዝ ዳውድ ደግሞ ከተማሪዎቹ መካከል ችሎታ ያላቸውን እየመረጡ እንዲያስተምሩ በየት/ቤቱ በየእስርቤቱና በየሆስፒታሉ በመላክ በ፲፱፻፵ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር በመስማማት እየተከፈላቸው ለምዕመናን በሬዲዮም መስበክ እንደጀመሩ ይገልፃል፡፡

በም.ኅ.መ.ገዳም በሚገኝ ፋይል ቁጥር፩ተራ ቁጥር ፴፬ ላይ ቤተማኅበር በኦርቶዶክሳውያን የተቋቋመ የሚል ግልፅ ያልሆነ ማስታወሻ (ደብዳቤ) አለ ይኹንና ስለምንነቱ የሚገልፅ ተጨማሪ መረጃ የለውም፡፡ ይህ ማኅበር ግን በዘላቂነት የቀጠለ አይመስልም፡፡

በ፲፱፻፷፯ዓ.ም የተካሔደውን አብዮትን ተከትሎ የተፈጠሩ የሕዝብ አደረጃጀቶች አ.ኢ.ወ.ማ አ.ኢ.ሴ.ማ. መ.ኢ.ገ.ማ የሚባሉ ማኅበራት በመፈጠራቸው በወቅቱ በነበረው መንግሥት ተፅዕኖ መንፈሳዊ ማኅበራት ማኅበር መባላቸው ቀርቶ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲባሉ በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን አባ ናትናዔል ለተምሮ ማሰተማር በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ጠቅሰውታል፡፡ይህንን ኃሳብ መምህር ታዬ አብርሃምም ያጠናክሩታል፡፡

ግንቦት ፭ ቀን “ቅዱስ ሲኖዶሰ በ፲፱፻፸ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ግንቦት ፲፬ ቀን ፲፱፻፸፪ ዓ.ም የወጣቶች ጉዳይ መምሪያ በጻፈው ደብዳቤ የወጣቶች መንፈሳውያን ማኅበራት አጠቃላይ ጉባኤ የሚለው የሃይማኖት አበው የሰንበት ት/ቤቶች የተምሮ ማስተማር ማኅበር የሚለው ስያሜ ተሽሮ ማንኛውም የሰንበት ትቤት እንዲባል ወጣት ማለትም ዕድሜአቸው ከ፲-፴ ዓመት ያሉት ብቻየሚ ደራጁበትእንዲሆን በቁጥር ፶፭/፰፭፩፫/፯፪በ፩፭/፩ዐ፯፪ በ አቶ መርስኤ ሃዘን አበበ የጠ/ቤት ክሀነት ሥራ አስኪያጅ በተፈረመ ደብዳቤ ተገልፆአል፡፡

ከፋሺስት ኢጣሊያ ድል መሆንን ተከትሎ የትምህርት ቤቶች መከፈት

ይህ ወቅት ሃገሪቷ ገና ወደ መረጋጋቱ ሙሉ በሙሉ ያልገባችበት ነበር፡፡በወቅቱ ስለነበረው ሁናቴ ብርሃንና ሠላም ጋዜጣ ሐምሌ ፲፮ ቀን ፲፱፻፴፱ ዓ.ም ባወጣው ጽሑፍበኢጣሊያ አጥቂነትና ግላዊነት አምስት ዓመት በሆነው ግፍ የኢትዮጵያ አገሮች ጠፉ ኢጣሊያ ያጠፋችው አገሩን ብቻ አይደለም የሰውን ልብ በጠበጠችው መንፈሱንም ገልብጣ የኢትዮጵያዊው አሳብ ተሽሮ ኢጣሊያዊ አሳብ እንዲተካ ጣረች በዚህ መካከል ይኖር የነበረው ሕዝብ ትክክለኛ ኑሮው ተናጋ የኑሮውም መሠረት አሳቡ ሁሉ ተናወጠ ሲል ይገልጸዋል፡፡

ብርሃኑ ድንቄም ቄሳርና አብዮት በሚለው መጽሓፋቸው ከኢጣሊያኖች ይዞታ በኋላ የኢትዮጲያ ህዝብ አሰተሳሰብ በፍጹም እንደተለወጠ ያልተገነዘበ አይገኝም ግን አለዋወጡ በግልጥ ፎርም እና አንጻር አልነበረውም …በዚያን ጊዜ ያለ ጥርጥር የአገር ፍቅር ስሜት በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ ነጻነትን አጥቶ የባዕድ ተገዥ መሆን ትልቅ ትምህርት ሆኖታል ሲሉ ገልጸውታል፡፡

በእንግሊዞች እርዳታና በአርበኞች ጽኑ ትግል የአምሥቱ የመከራ ዓመታት በሚያዚያ @7 ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር ቸርነት እንደተፈጸመ ለማገገም ስትል ወዲያውኑ ግንቦት ፪ ቀን ፲፱፻፴፫ ሚኒሰትሮቿን ሾመች፡፡ ሁለተኛው የትምህርት ቤቱ መከፈት ታሪክ የሚጀምረው ከ፲፱፻፴፬ ጀምሮ ነው በተለይ እሰክ ፲፱፻፶፯ ያለውን ለሚያካትተው የትምህርት ቤቱ ታሪክ ቀደም ሲል የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቁ የትምህርት መሣሪያዎችና መፃሕፍት ግብዓቶች ከአውሮፖ የሚመጡ ስለነበሩ ከፍተኛ ችግር ውሥጥ ነበር::

ይህንኑ ችግር ለመፍታት እሰከ ፲፱፻፴፰ ዓ.ም መጠበቅ ግድ ነበር ፡፡ በ፲፱፻፴፰ ዓ.ም ዶክተር ማት የተፈሪ መኰንን ት/ቤት ዳሬክተር ሲሆኑ አስፈላጊ የትምህርት መሣሪያዎችን ከአሜሪካንና ከእንግሊዘ አገሮች ገዝተው እንዲያመጡ ተላኩ፡፡ ይኽም ወቅት ፪ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ አግኝቶ ስለነበር የሳይንስ መሣሪያዎች/ኘሮጀክተር/ ፊልም የሚታይባቸው ዕቃዎች/ላንቴርን ስላይድ/ የፊልም ጥቅሎች በትምህርት ቤት አስፈላጊ የነበሩ መማሪያዎችን ለማግኘት ተቻለ (ያልታተመ ጥናታዊ ጽሁፍ ገፅ ፲፱)፡፡

በ፲፱፻፴፱ና በ፲፱፻፵ ት/ቤቱ በጣም የተሰፋፉበት ዘመን ነበር፡፡ በ፲፱፻፴፱ የተማሪዎች ብዛት ፲፪፻፲ ሲሆን በሙሉ ወንዶች ነበሩ (ያልታተመ ጥናታዊ ጽሑፍ ሠንጠረሽ ፫/ሀ/) ፡፲፱፻፴፮-፷፫ የት/ቤቱ እንቅስቃሴ ይካሄድ የነበረው በካናዳውያን/Jesuits ወይንም ኢየሱሳዊያን የካቶሊክ መምህራን ነበር፡፡ የትምህርት አሰጣጡንም ሆነ የተማሪዎቹዲስፕሊን በካናዳውያኑ ይሠራ ስለነበር የአሠራሩ ባህርይ በውጭ ዜጐች ሙሉ ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡የአማርኛ ቋንቋን ሳይቀር የሚያስተምሩት ካቶሊካውያኑእንደነበሩ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ ተናግረዋል፡፡

ፋና ወጊው ወልደ ሰማዕት ገብረወልድ

በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከ፲፪፻፲ ተማሪዎች መካከል ለትምህርት ከከተሙት አንዱወልደሰማዕትገብረወልድ (አሁን ደጃዝማች) ነበሩ፡፡ ትምህርት ቤቱን የተቀላቀሉት በ፲፱፻፴፮ ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በአስተማሪነት የነበሩትን መምህራንን ደጃዝማች ወ/ሰማዕት ሲገልጹአቸው በየሙያቸው ጥልቅ የሆነ ዕውቀት የነበራቸው በትምሀርት ክፍልና ከክፍል ውጪ ተማሪውን ለራሱም ሆነ ለአገር ዕድገት የሚጠቅምናአገሩን የሚወድ ዜጋ  እንዲሆን የሚያዘጋጁት ነበሩ፡፡ ተማሪዎች በትምህርትና

በሥነምግባር ታንጸው ጽኑ የአገር ፍቅር አድሮባቸው እውነተኛ የሕዝብ አገልጋዮች ሆነው አገራቸውን ማበልጸግ እንዲችሉ ለማድረግ ይሰሩም ነበር፡፡

ተማሪዎችን የሚያስተምሩ የነበሩ እነዚህ መምህራን አቻየማይገኝላቸው ከፍተኛ ዕውቀት የነበራቸው ምሁራንም ነበሩ፡፡ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ክፍሎች ለሚማሩት ተማሪዎች በክፍል ከሚያስተምሩት መደበኛ ትምህርት በተጨማሪ መምህራን እንደ አማካሪዎች ሆነው ለየአንዳንዳቸው ተመድበውላቸው በሳምንት ሁለት ቀን ማታ ወደ አማካሪያቸው ቤት እየሄዱ ለሁለት ሰዓት ያህል ስለአገር ፍቅርና ሥነምግባር ከትምህርት ቤት ጨርሰው ሲወጡም ሕዝብንና አገርን ማገልገል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይህንንም ሲፈጽሙ በታማኝነትና በትጋት መሥራት እንዳለባቸው በልዩ ልዩ ዘዴዎች ይመክሯቸውና ያስተምሯቸው ነበር፡፡ አማካሪዎቻችው ሌላው ቀርቶ ወደፊት ሲለሚመሰርቱት ጋብቻና ስለሚኖሯቸውልጆች አሰተዳደግ ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ እንዴት አድርገው እየተንከባከቡ ማሳደግ እንደሚገባቸው ልጆች ከወላጆቻቸው ስለሚማሩት ጭምር ይነግሯቸው እንደነበረ ይገልጸሉ ፡፡ይህንንም አባባል ቀሲስ ታደሠ መንግሥቱ ቃል በቃል በሚመስል ሁኔታ በቃለ ምልልሳቸው ላይ ደግመውታል፡፡

ደጃዝማች ሲቀጥሉም በዚያን ጊዜ በትምህርት ቤት ከተማሯቸው ትምህርቶች ያላነሰ በተለይ ስለ መልካም አስተዳደርና የአገር ፍቅር በልጅነታቸው ከአባታቸው ካገኙት ምክርና ትምህርት በተጨማሪ ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስተማሪዎቻቸው ከፍ ያለ ግንዛቤና ጥቅም አግኝተውበታል፡፡

መንፈሣዊ ተዐምርና የፕሬቮ ምስጢራዊ ሪፖርት

ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረወልድ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሲማሩ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ከእርሳቸው ጋር የኖረናሳይናገሩ ማለፍ የማይችሉት  አንድ የተፈጠረ አስደናቂ መንፈሳዊ ተአምር አለ ሲሉ ለዚህ ጥናት አቅራቢ እንባ እየተናነቃቸው ሲገልጹ“ እግዚአብሔር እኔን ይጎትተኛል እኔ ግን እሸፍታለሁ”በማለት  እነዚያ ብለው በመጀመር ስለ ኢየሱሳውያን ጄስዊቶች ቀጥለዋል፡፡

እነዚያ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የውጭ አገር ተወላጅ አስተማሪዎቻችን የሚኖሩት እዚያው ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ በጋራ እራት በልተው ወደ ጋራ ጸሎት ቤታቸው ሄደው ጸሎት ካደረሱ በኋላ ሲጨርሱ ወደ የመኖሪያ ቤታቸው የመሄድ ልማድ ነበራቸው፡፡

አንድ ቀን ግን  ማታ ቀደም ብዬ አማካሪዬ ሆኖ ወደ ተመደበልኝ መምህሬ ወደ ነበረው ሚስተር ፕሬቮ መኖሪያ ቤት ስሄድ አማካሪዬ ከጋራ ጸሎት ቤት ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ እቤታቸው ደረስኩ፡፡ ተማሪዎች ወደ የአማካሪዎቻችን ቤት ስንሄድ በቤት ውሰጥ ከሌሉ እስኪሚመጡ ድረስ ሻይ አፍልተን በዚያን ጊዜ ለእኛ ተማሪዎች ብርቅ የነበረውን ደረቅ ብስኩት በሻይ እየተመገብን አማካሪያችንን መጠበቅ የተፈቀደልን ቢሆንም ያ ዕለት እንደገባሁ ሚስተር ፕሬቮ ስላልነበሩ ሐሳቤ ወደ ሻይ ማፍላቱና ደረቅ ብስኩት መመገቡ ሳይሆን ምን እንደገፋፋኝ ሳላውቀው ወደ አማካሪዬ ጠረጴዛ ዓይኔን ወርወር ሳደርግ በመጻፍ ላይ የነበረ ሪፖርት  ተዘርግቶ አየሁ፡፡ ውስጤ ወደዚያው ደብዳቤ ስለመራኝ ወደ ጠረጴዛው ሄድኩና ያን ተጽፎ ያልተደመደመውን ሪፖርት ቁጭ ብዬ ማንበብ ጀመርኩ ሲሉ ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገልጸዋል፡፡

ደብዳቤው የተጻፈው በፈረንሳይኛ ቋንቋነበር፡፡ ከፍተኛ ክፍል ለነበሩት ተማሪዎች ከእንግሊዘኛው እኩል ፈረንሳይኛም ይማሩ ስለነበረ በፈረንሳይኛ የተጻፈውን መገንዘብና ምንነቱን ማወቅ አልተሳናቸውም፡፡ ጽሑፉን ማንበብ በመጀመራቸው ከአንዱ መስመር ወደሌላው በሄዱ ቁጥር መላ ሰውነታቸውን እየወረራቸውና ፍርሀት ፍርሀት እያላቸው ተጽፎ ያልተቋጨውን ሪፖርት በቁጭትና በመባባት ስሜት ሆነው አንብበው ጨረሱት፡፡

ሰውነታቸው  በፍርሀት እየራደ ሳይለቃቸው አማካሪያቸው ሳይመጣ በፍጥነት ከቤታቸው ወጥተው ወደ መኝታ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ጥቅልል ብለው ለመኝታ ቤት ጓደኞቻቸውም ሳይነግሯቸው ተኝተው ማልቀስ ጀመሩ፡፡ ወደ አማካሪያቸው  ቤት ሲሄዱ ባንድ መኝታ ክፍል አምስት ያህል ሆነውና አብረው ከሚኖሩት አራቱ የመኝታ ቤት ጓደኞቻቸው እነ ታደሰ መንግሥቱ ወርቁ ተፈራ ሽፈራው መታፈሪያ ና ዶ/ር አክሊሉ ኃብቴ ዘወትር ከእራት በኋላ በተማሪዎች ዲን በሚስተር ዚፈል ተቆጣጣሪነት ይካሄድ በነበረው ከመመገቢያ ቤታችውና ጥናት ቦታ ሄደው የነበሩት ጓደኞቻቸው የጥናቱ ሰዓት ማለቂያ ደርሶ አንድ ባንድ አየተመለሱ ይመጡ ጀመር፡፡ ከአማካሪያቸው ሚሰተር ፕሬቮ ቤት ለምን ቀደም ብለው እንደተመለሱና ለምንስ ተጠቅልለው እንደተኙ በመጠየቅ ተነስተው ምክንያቱን እንዲነግሯቸው ቢጠይቋቸው  ሳይነግሯቸው ጥቅልል ብለውእንደተኙ ሲያለቅሱ አደሩ፡፡

በአማካሪያቸው በሚስተር ፕሬቮ መኖሪያ ቤት ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ያጋጠማቸውና ያነበቡት ያ በመጻፍ ላይ የነበረ ያልተደመደመ ሪፖርትና ደብዳቤ የተጻፈው ካናዳ ለሚገኘው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መምህራን ለመጡበት የኢየሱሳውያን (የጄዝዊትስ) ማዕከል ነበር፡፡ በመጻፍ ላይ የነበረው ደብዳቤ የሚናገረው ግራኝ መሓመድ ኢትዮጵያን በወረራት ዘመን ለዕርዳታ ከመጡት የፓርቹጋል ወታደሮች ጋር፣ ከዚያም በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስለገቡትና አጴ ሱስንዮስና መኳንንቶቻቸውን ወደ ካቶሊክ እምነት ስለ ለወጧቸው እነ ጴጥሮስ ፖኤዝ ሜንዴዝና ሌሎች የኢየሱሳውያን መነኮሳት ነበር፡፡ እነዚያ የኢየሱሳውያን መነኮሳት ንጉሠ ነገሥቱንና መኳንንቶቻቸውን ወደ ካቶሊክ እምነት ለውጠው የቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ካቶሊክ እምነት ለመለወጥ ጥረት ሲያደርጉ በተለወጡትና ባልተለወጡት ኢትዮጵያውያን መካከል ብዙ ደም ያፈሰሰ ጦርነት እንዲካሄድና ብዙ ደም እንዲፈስ ምክንያት የሆኑትን የጄዝዊት መነኮሳት ስለፈጸሙት ስሕተትና መነኮሳቱ ምክንያት ሆነው በተሰሩት የጎንደር ቤተ መንግሥት ታላላቅ ሕንጻዎች፣ ድልድዮችና ሌሎች ስራዎች አጓጉተው ወደ ካቶሊክ እምነት የለወጧቸውን አጼ ሱስንዮስም ደጋግሞ የሚያነሳ ነበር፡፡

ደጃዝማች በዚያን ጊዜ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የሚያውቁት ነገር ስላልነበረ እነፓኤዝናሱስንዮስ እነማን ናቸው? መምህራኖቹ እንደነ ጴጥሮስ ፖኤዝ ና አልፎንስ ማንዴዝ ቸኩለው እንዳይሳሳቱ በጥንቃቄ የሚሰሩት ስራ ምንድን ነው? የሚሉትንና በደብዳቤው የተጠቀሱትን ሌሎቹንም ጉዳዮች ሲያወጡና ሲያወርዱ ሲበሳጩና ሲያለቅሱ አድረው ጠዋት ወደ ትምህርት ክፍል መግባቱን በመተው ለአዳሪ ተማሪ ያለፈቃድ ወደ ትምሀርት ቤቱ መግባትና መውጣት የማይቻለውን ዋናውን በር ትተው ፣ ከትምህርት ቤቱ በስተሰሜን በኩል ባለው የሽቦ አጥር በመሹለክ ጥቅጥቅ ባለው የባህርዛፉ ጫካ ውስጥ አቆራርጠው ከእንጦጦ ከአሜሪካን ኤምባሲ በኩል ቁልቁል በሚመጣው ጎዳና በመግባት ፒያሳ በኪንግ ጆርጅ ቡና ቤት ተርታ በምዕራብ በኩል ወደሚገኘው ጃኖፖሎስ መጽሐፍት መሸጫ ሱቅ ገሰገሱ፡፡

መጽሐፍት መሸጫው ሱቅ እንደደረሱም፤ የሚገርም ተአምር ገጠማቸው፡፡ ይኸውም ገና ወደ መጽሐፍት መሸጫው ሱቅ ሳይገቡ ከመስታወት መስኮቱ ላይ የተደረደሩትን መጻሕፍት ሲመለከቱ በመጽሐፉ ጠንካራ ልባስ ላይ የተሸፈነ ሌላ ጥቁር የወረቀት ሽፋን ላይ በላዩ ሰንደቅ ዓላማ ያነገተ ቀይ ሞአ አንበሳ የሚገኝበት ርዕሱ “የአቢሲኒያ ታሪክ የሚል መጽሐፍ ተመለከቱ፡፡ ወደ ውስጥ ገብተው ሻጩን መጽሐፉን እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ኢንዴክሱን እያገላበጡሲያነቡ የሚስተር ፕሬቮ ደብዳቤ ውስጥ የተጠቀሱትን ስሞች ሁሉንም በማግኘታቸው መጽሐፉን ገዝተው ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ ማንም ሳያየቸው በወጡበት የሽቦ አጥር ሾልከው ይገባሉ፡፡

ወደ ትምሀርት ቤቱ ተመልሰው በገቡበት ሰዓት ተማሪው ሁሉ በየትምህርት ክፍሉ ገብቶ የሚማርበትና ግቢው እረጭ ያለበት ጊዜ ስለነበረ መኝታ ክፍላቸው አንሶላ ውስጥ ገብተውየገዙትን መጽሐፍ ኢንዴክሱን እየተመለከቱየሚፈልጉትን ርዕስ በመምረጥ ማንበብ ጀመሩ፡፡ መጽሐፉን ወደ ውስጥ ገብተው ሲያነቡ በግራኝ ወረራ ዘመን ለእርዳታ ከመጡት የፓርቹጋል ወታደሮች ጋር መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡትና በኋላም የመጡት አፄ ሱሱንዩስንና መኳንንቶቻቸውን ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲለወጡ ባደረጉት ምክንያት በኢትዮጵያውያን መካከል የተከሰተውን ሃይማኖታዊ ጦርነት፣ የሕዝብ እልቂትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውድመት በተገነዘቡት ቁጥር ሆዳቸው እየባባ ትላንት ማታና ሌሊት ሲያለቅሱ ያደሩት እየተባባሰ ስለሄደና በጣም አዝነው ስለነበረ፣በተጨማሪም ጠዋት ክፍል ስላልገቡና ምሳም ላይ በመመገቢያ ክፍል ስላልተገኙ፤ በመኝታ ቤትም ሆነ በትምህርት ክፍል አብረው ከሚማሩት ውስጥ የቅርብ ጓደኛቸው የነበረው ሽፈራው መታፈሪያ መኝታ ቤት እንዳሉ ለማየት ይመጣሉ፡፡ በጣም አዝነውእያለቀሱ ሲያገኛቸው ደንግጦ ምክንያቱን ይጠይቃል፡፡ ደጃዝማችም ትናንት ማታ አማካሪያቸው ሚስተር ፕሬቮ ቤት ሄደው ካነበቡት ደብዳቤ ጀምሮ ያለውን፣ ና ከገዙት መጽሐፍም ያነበቡትንና የተሰማቸውን የመረበሽ ሁኔታ ሲነግሯቸው እሳቸውም ማልቀስ በመጀመራቸው አብረው ብሶታቸውን ይወጡ ጀመር፡፡ ከዚያም ጉዳዮን በምስጢር ይዘው ለቅርብ ጓደኞቻችው ለመንገር ተስማሙ፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩን  አንድ በአንድ የነገሯቸው የቅርብ ጓደኞቻቸው ወርቁ ተፈራ (በኋላ ቀ.ኃ.ሥዩኒቨርስቲ የሕግ አስተማሪና የሕግ ፋክልቲ ዲን የነበሩት)፤ ታደሰ መንግሥቱ ሽፈራው መታፈሪያና ለሌሎችም ለእያንዳንዳቸው የተነገራቸው ሁሉ ተሰባስበውና ጉዳዩን በምስጢር ይዘው ቁጥራቸውን ዐሥራ ሁለት በማድረግ ዘዴ ለመፈለግና ስራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን  ህቡዕ ማኅበር አቋቋሙ፡፡እነዚህም:-

                ፩ አበበከበደ

                ፪ አባተመንክር

                ፫ አክሊሉኃብቴ ( ዶ/ር)

                ፬ አሰፋተክለሥላሴ

                ፭ ወልደሰማዕትገብረወልድ (ደጃዝማች)

               ፮ ወርቁተፈራ

               ፯ መኮንንዋሴ

              ፰ ስዩምወልደአብ *

              ፱ ተሰማአባደራሽ ( ኮሎኔል)

              ፲ ታደሰመንግሥቱ (ቀሲስ)

              ፲፩ ታደሰመታፈሪያ ና

              ፲፪ ሽፈራውመታፈሪያ ነበሩ፡፡

*ተራ ቁጥር ፲፩ን ደጃዝማች ወልደሰማዕት ሊያሰታውሷቸው አልቻሉም ፐሮፌሰርመሥፍን ወልደማሪያም ይሆኑ እንደሆነ ተጠይቀው እርሳቸው በኋላ ላይ ተጨምረው ይሆናል እንጂ ከ፲፪ቱ ውስጥ የሉበትም ብለው ለዚህ ጥናት አቅራቢ ነግረውታል፡፡ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ ማርያምን ለመጠየቅ የተደረገውጥረትአልተሳካም፡፡

*የስም አፃፃፋቸው አ በ ገ ደ……. የሚለውን የፊደል ቅደም ተከተል መሰረት በማድረግ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አባላት በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም ህቡዕ ማኅበር እንዳቋቋሙ ታደሰ መንግሥቱ በቃለ ምልልስ ላይ በምስልና በድምጽ ሁሉንም በስም ባይጠቅሱአቸውም የተወሰኑትን በመግለጽ ያረጋገጡት ሲሆን አበበ ከበደም በተለያየ ጽሑፎች ላይ በ፲፱፻፴፱ መሰባሰብ እንጀመሩ ይገልጹታል፡፡ ደጃዝማች ግን ሁኔታውን ከጳጳሳት ሹመት ጋር በማያያዝ በ፲፱፻፵ ይመስለኛል ይላሉ፡፡ ይሁንና አበበ ከበደ በእንግለዝኛ ለእርዳታ ማሰባሰቢያ ዐላማ በጻፉትና ና በፈረሙበት ደብዳቤ እ.ኤ.አ  በ፲፱፻፵፯ እንደ ተጀመረ ስለገለጸ ይህ ደግሞ ፲፱፻፴፱ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡የተምሮ ማሰተማር ማኅበር ዓመታዊ መጽሄቶች ላይ በተደጋጋሚ ፲፱፻፴፱ በሚል ተገልጾአል፡፡ ምን አልባት ኅቡዕ ማኅበሩ ተሰብስቦ ስራውን ጀምሮ በወቅቱ ጉዳዩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እስኪደርስ ወራትን ፈጅቶ ወደ ፲፱፻፵ ተሻግሮ ይሆናል፡፡ በበርካታ ጽሁፎች ላይና ቃለመጠይቅ ላይ እንደተገለጸው ግን  በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም ነው፡፡(የተምሮ ማስተማር ማኅበር ፲ኛ ና ፲፭ኛ ዓመታዊ በዓል አከባበር መጽሔት)

ኅቡዕ ማኅበሩ እየተሰባሰበ መመካከር እንዲችል፣አንድ ዘዴ መፈጠር ነበረበት ምክንያቱም የሚሰበሰቡበት ዐላማ ከታወቀ ከትምህርት ቤቱ መባረርን ከማስከተሉም በላይ ንጉሠ ነገሥቱ ከሠሙም በልመናና በእርዳታ በብዙ ድካም የመጡትን መምህራን ማስቀየም ጉዳቱ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነበር፡፡

ስለዚህም የተገኘው መላበትምህርት ቤቱ የሚገኙትን መጥፎ ጠባይ ያላቸውን  የመኳንንት ልጆችና ሌሎች በትምህርትየሚያስቸግሩትን ተማሪዎች ለመምከርና የተጣሉትን ለማሰታረቅ እንድንችል መሰብሰብ እንዲፈቀድልን በማለት ዲን የነበሩትን ሚስተር ዚፈልን መጠየቅ ነበር፡፡ እሳቸውም አንዳንድ ተማሪዎች የአልኮል መጠጥ እየጠጡ ረብሻ ና ድብድብ ይፈጥሩ ስለነበር ሃሳቡን በደስታ ተቀብለው “ብትፈልጉ ከትምህርት ክፍሎች አንዱን መርጣችሁ ወይም በምትመርጡት መኝታ ቤታችሁ ሆናችሁ የምክር አገልግሎት መስጠት ትችላላችሁ” ብለው ፈቀዱላቸው ፡፡ ለማንኛውም አመች ሆኖ የተገኘው መኝታ ቤታችው ስለሆነ ፕሮግራም በማውጣት መጥፎ ጠባይ የነበራቸውንና ያስቸግሩ የነበሩትን ከመኳንንት ልጆች እንደነ ጃራ መሥፍንና ስለሺ በዛብህ ያሉትንና ሌሎች አስቸጋሪ የነበሩትን ልጆች እየተጠሩ ለስም ያህል ለጥቂት ደቂቃዎች የምክር አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡

ይሁን እንጂ ረዘም ያለውን ሰዓት እየወሰዱየሚመካከሩትናየሚያጠኑት ድብቅ የነበረውን ዐላማቸውን እያስፋፉ የነበሩትን ኢየሱሳውያንን ከኢትዮጵያ ለማባረር የሚችሉበትን ዘዴ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ዓላማቸውን የሚያሳኩበት ጥናት እያካሄዱ በሚደንቅና በማይታመን ሁኔታ ዓላማቸውን ካስረዷቸውና አዝነው ሃሳባቸውን የተቀበሉዋቸው በዚያን ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር የነበሩትን አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ እንዲሁም አባ መልዕክቱ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስተ ብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛ ፓትርያርክ የሆኑትን እና ሌሎችን በማሳመንና ስለ ኢየሱሳውያን ታሪክ አጥርተው የሚያውቁትን  በሌሎች ሃገሮች እምነታቸውን ለማስፋፋት መንግሥት እሰከመገልበጥ ደረጃ እንደሚደርሱ በመግለጥ ከፍተኛ ሥራ የሰሩላቸውን በወቅቱ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልዩ ጽሕፈት ቤት ያገለግሉ የነበሩትንና አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩትን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሕንዳዊውን ሚስተር ፓል በርጊስ የማህበሩ አባላት እንዲሆኑ በማድረግ ማኅበራቸውን አጠናክረው ዓላማቸውን ማሳካት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ፡፡

በትምህርት ቤቱ መኝታ ቤታቸው ለስም ያህል ለተማሪዎች የምክር አገልግሎት እንሰጣለን በሚል ይሰብሰቡ እንጂ ዋናው ስብሰባ ግን እሑድ እሑድ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ግቢ ውስጥ በምዕራብ በር ሲገባ በግራ በኩል በሚገኘው አባ መልእክቱ( በኋላ አቡነ ቴዎፍሎስ )በሰጡአቸው ድብቅ የስብሰባ ቤት ነበር፡፡

ማኅበሩ ከዓመት በላይ ጥናቱን ሲያካሄድ ቆይቶ አጠናቀቀና ጉዳዩን በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለመግለጥና ሊቃውንቱ እንዲሰበሰቡላቸው ለመጠየቅ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ ይኖሩ ወደነበሩት የእጨጌ ገብረጊዮርጊስ በኋላ አቡነ ባስልዮስ ተብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትርያርክ ዘንድ ሄደው ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡ በዚያን ወቅት አጋጣሚ ሆኖ እሳቸው ከነ ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ ጋር ስለ ጳጳሳት ሹመት ለመነጋገር ወደ አሌክሳንድሪያ ለመሄድ ተነስተው ስለነበረ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ቢሰሙ ስለሚያዝኑና አደገኛም ስለሚሆን በአባ መልዕክቱ ሰብሳቢነት መጀመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ሊቃውንት ብቻ በምስጢር ተሰብስበው በሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ላይ እንዲነጋገሩ “በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሊቃውንት ይሰብሰቡልን” የሚለውን ሐሳባቸውን ለጊዜው እንዲተው ለምነው ና አግባብተውእንዲስማሙ ተደረገ፡፡

ገብረጊዮዎርጊስ ጋር በተስማሙት መሠረት፤ እሳቸው ወደ አሌክሳንደርያ ሄዱና በአባ መልዕክቱ ሰብሳቢነት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ሊቃውንት በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በምዕራብ በኩል በሚያስገባው በር ላይ በግራ በኩል ባለው እስካሁን በሚገኘው አዳራሽ ውስጥ እጅግ ስሜታዊ የሆነ ና በሐዋርያት መልክ በአስራ ሁለት አባላት የተሰባሰቡትን ማኅበርተኞች ጉባኤተኞቹና የአዲስ አበባ ሊቃውንቱን ሁሉ እንባ ያራጨ ስብሰባ ተካሄደ፡፡

በዚህ በድንገት በተከሰተ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እዚህ በአዲስ አበባ  ከተማ በሚገኙት ገዳማትና አድባራት የሊቃውንት ጉባኤ በኋላ የማኅበሩ ምስጢር እየሾለከ ወጣና አንዳንድቀንደኛ የማኅበሩ አባላት ናቸው ተብለው በተጠረጠሩት ላይ ምክንያት እየተፈለገ ከትምሀርት ቤት እንዲወጡ ሌሎቹም ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እዲዛወሩ ሲደረግ ከተባረሩት ተማሪዎች ውስጥ አንዱና  የመጀመሪያው ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ ሆኑ፡፡ ሆኖም፤ የትምህርት ጊዜያቸው ዐንድ ዓመት ወደ ኋላ ቢጓተትባቸውምቀደም ሲል ዐላማቸውን በመረዳት የማኅበሩ አባል ያደረጉአቸውን  የዚያን ጊዜው የትምህርት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ኮተቤ ቀ.ኃ.ሥ. ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት ስለአስገቧቸው ከዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡

ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ወደ ሌሎች ትምሀርት ቤቶች እንዲዛወሩ የተደረጉትና የተባረሩትም በአቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ዕርዳታ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲገቡ ስለተደረጉ፣ ማኅበሩ በድብቅ ስብሰባውን ማካሄዱን መቀጠል ብቻ ሳይሆን፤ በየትምህርት ቤቱ የተበተኑት በያሉበት ቅርንጫፍ ማኅበር ስላቋቋሙ ማኅበሩ ተጠናክሮ ዋናውን ሚስጢር ለሰፊው የተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተማሪዎች ሳይገልጹ በደፈናው አስተማሪዎች የተማሪዎችን መብት አያከብሩም፤ ለሃይማኖት ወገኖቻቸው ያደላሉ፤ ወዘተ በሚሉ ተልካሻ ምክንያቶች በጄዙዊቶቹ አስተማሪዎችና በሚደግፉዋቸው ተማሪዎች ላይ አድማ እንዲቀሰቅሱ ተደረገና ከፍተኛ ብጥብጥ ተነስቶ ትምህርት ቤቱን ማስተማሩን ከማቋረጥ ደረጃ ላይ አደረሰው፡፡

ይህንን ጊዜ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ስለተደረገው ከፍተኛ ረብሻ ከኅቡዕ ማኅበሩ አባላትውጪ ትክክለኛ ምክንያቱን የሚያውቅ አልነበረም ፡፡ዶ/ር አክሊሉ ኃብቴም ለዚሁ ጥናት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ጉዳዩ የሃይማኖት እነደነበር ተቃውሞውንም ይመሩት የነበረው የዚሁ ኅቡዕ ማህበር አባላት እንደነበሩ በስም በመጥቀስ አረጋግጠዋል፡፡ መምህራኖቹ በአደባባይ አንዳችም የኃይማኖት ትምህርት የማይሰጡ ሲሆን እንዲያዉም በተቃራኒው ሁሉም ተማሪ በሚያምንበት ቤተ እምነት እንዲሔድ ያበረታቱ እነደነበር ነገር ግን አንዳንድ ተማሪዎችን  በመነጠል በግልይሰበኩ እንደነበር ዶ/ር አክሊሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

ኢንጅነር ታደለ ብጡል መጽሓፈ ውይይት ከከበደ ሚካኤል ጋር በሚል በጻፉት መጽሓፍ በወቅቱ የተነሳውን ረብሻ ምክንያቱን ያውቁ እንደሆነ ለከበደ ሚካኤል አቅርበው ከበደ ሚካኤልም እንደማያውቁና ረብሻው ግን ንጉሠ ነገሥቱን እስከመያዝ የደረሰ የመረረ ተቃውሞ እንደነበር ጃንሆይም እንዳይመጡ የትምህርት ቤቱ ዴሪክተር ሚ/ር ዙፌል  እንደጠየቃቸው ተናግረው በተሳትፎው ውስጥ እነ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም እንደነበሩበት ገልጸዋል፡፡ፕሮፌሰር መሥፍን  በወቅቱ ስለነበረው ረብሻ ና ተማሪዎቹ ያነሱት ጥያቄ መምህራኖቹ አባቶቻችንን ሰደቡብን የሚል ነበር ሲሉ በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ጠቅሰውታል፡፡

ይህንን ተቃውሞና ረብሻ በመጀመሪያ ባለሥልጣኖች አድማውን ለማብረድ ሞክረው ስላቃታቸው ሌላው ቀርቶ ከቤተ መንግሥት አባ ሐና ጂማና የዕልፍኝ አስከልካዮች ወደ ትምህርት ቤቱ እየሄዱ አድማውን ለማብረድ ሞክረው ስለተሳናቸው፤ ንጉሠነገሥቱ ራሳቸው ወደ ትምህርት ቤቱሄዱ ሲሉ የሚገልጹት ደጃዝማች አድማውን ለማብረድ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተገኝተው የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ሌት ከቀን ሲጥሩ፤ ተማሪዎች ምኞታቸውን የሚያሰናክል ችግር በመፍጠራቸው ተበሳጭተው ስለነበረ፤ ለንጉሠ ነገሥቱ የአድማውን ምክንያት ለማስረዳት ከሞከሩት ውስጥ አንዱ ተማሪ ዮሐንስ መንክር ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርቦ ሲናገር፤ ንጉሠ ነገሥቱ ተናደው በጥፊ ሲመቱት ሌላውን ያልተመታውን ሁለተኛውን ጉንጩን አመቻችቶ ስላቀረበላቸው ሊመቱት የቃጡበትን እጃቸውን እንደመለሱ እስካሁን እንደ ተረት ሆኖ የሚነገር ሆኗል ይላሉ፡፡ ይህ ሲሆን በዚያን ጊዜ ደጃዝማች ኮተቤ ቀ.ኃ.ሥ. ሁለተኛ ደረጃ ይማሩስለነበር ተማሪዎች ባነሱት ከባድ ረብሻ ወቅት የሆነውን በትክክል ባያውቁትም እንደተከታተሉት ከሆነ አድማው እንደተረጋጋ ጥቂት ተማሪዎች ወደጠቅላይ ግዛቱና አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኙ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ሳይባረሩ አልቀሩምብለዋል፡፡

አበበ ከበደ የተምሮ ማስተማር አዳም(፲፱፻፳፬-፲፱፻፸፩)፤፤
(ሥመ ክርስትና ገብረኪዳን፤፤)

አቶ አበበ ከበደ(ገብረ ኪዳን) ከህይወት ታሪካቸው የዚህ ጥናት አቅራቢ እንደተረዳው ከስመ ጥሩ አርበኛ ከፊታውራሪ ከበደ ወልደ ጊዮርጊስና ከወ/ሮ ዐመለወርቅ ኢየሱስ በ፲፱፻፳፬ ዓ/ም አርሲ ክ/ ሀገር ተወለዱ፡፡

እንደ ብዙዎች ልጆች ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ን.ነ ዘኢት. የአርበኛ አባታቸውን ውለታ በማስታወስ በቀድሞው ተፈሪ መኰንን ት/ቤት በአዳሪነት እንዲማሩ አደረጉ፡፡ በዚሁ ት/ቤት እስከ ፲፱፻፵፫ ዓ/ም ድረስ ተምረዋል፡፡በ፲፱፻፵፬ ሐረር መመህራን ማሠልጠኛ ት/ቤት ገብተው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ ቀ.ኃ.ሥ ኮከበ ጽባሕ ይባል በነበረው ት/ቤት ተመድበው ሲያስተምሩ ባሳዩት ችሎታና ቅን አገልግሎት ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው ወደ አሜሪካ በመሔድ ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር ውሰጥ ተመድበው በመጀመሪያ የዕደ ጥበብ ማዕከል ኃላፊ ቀጥሎም የአሁኑ ብሔራዊ ቴያትር (የቀድሞው የቀ.ኃ.ሥ.ቴያትር) ዲሬክተር በመሆንም አገልግለዋል፡ ኃላፊነታቸውን በሚያስመሰግን ሁኔታ በመወጣታቸው በለንደንየትምህርት አታሼ ሆነው ተሾሙዋል ፡፡ በዚህም ኃላፊነታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ አበይት ተግባራትን በማቀድና በማከናወን ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እንዳበረከቱ ታውቋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በመጀመሪያ ኢየሱሳውያን በመባል የሚታወቁትን የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መምሕራን የሚያደርጉትን ቅሰጣ በጽኑ በመቃወም የተማሪውን ተቃውሞ መርተዋል፡፡ ደጃዝማች ስለ አበበ ከበደ  ሲገልጹ ከሁላችንም በጣም ልጅ እርሱ ነበረ፡፡መንፈስ ቅዱስ የቀረበው የሚሠራው ሁሉ የሚሳካለት ተምሮ ማሰተማርን በመመስረት ቀዳሚው ሰው ነበር ከታደሰ መንግስቱ ጋርም የቀረቡ ጓደኛሞች ነበሩ ይላሉ፡፡

ኘሮፎሰር መስፍን ወልደማርያም ሥልጣን ባህልና አገዛዝ ፖለቲካና ምርጫ በሚል በ፳፻፫ ዓ.ም ባሳተሙት መፅሐፈ አበበ ከበደን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የቀርብ ጓደኛዬ ነበር በጣም ርኅሩኅና ሃይማኖተኛ ሰው ነበር ብለው ከስር በኅዳግ አበበ ሁሌም በበጎ አድራጐት ሥራ ላይ አካል ጉዳተኞችንና ደሀዎችን ለመርዳት ሲጥር የነበረ ሰው ነው ከነደጃዝማች ካሣ ወልደ ማርያምና ከነ አቡነ ቴዎፍሎስ ጋር በደርግ የተገደለ ነው ብለዋል፡፡ዶ/ር አክሊሉ እኔ እስከ ማስታውሰው አበበ ከበደ ማህበሩን ለመመስረት በዋናነት ወዲያ ወዲህ ከሚሉት ውስጥ ሲሆን  ለኔም ስለ ማህበሩ የነገረኝ እርሱ  ነው፡፡ዘመናዊ ትምህርት ና መንፈሳዊ ትምህርት በአንድ ላይ ማስኬድ ይቻላል የሚልዘመናዊ መሆን የጥንቱን የሚያስንቅ ሳይሆን የሚያስወድድ ነው የሚል ዕምነት የነበረው ጨዋ ሰው በመንግስት ኃላፊነት እንኩዋን ሆኖ ማኅበሩን በግለሰብ ደረጃ ና በከፍተኛ ደረጃ ይከታተል ነበር ሲሉ ለዚህ ጥናት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ማህበሩን አንደመሠረቱት የሚታመኑ በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም መጀመረያ ፲፪ ሆነው ከተቋቋሙት አባላት መካከል በተለያየ ምክንያት ትምህርት ቤቱን ለቀው ሲሄዱ ፭ (፮) የሚሆኑትና ስማቸው ከዚህ በታች የተጠቀሱት ተማሪዎች በ አበበ ከበደ አሰባሳቢነት ከዚሁ ዘመናዊ ት/ቤት መከፈት ጋር በተያያዘ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ማኅበራትን መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ለተምሮ ማስተማር ማኅበር መመሥረት ጥንስስ የሆነውየተጣሉትን ማስታረቅና መፅሐፈ ቅዱስ ጥናት በሚል ሽፋን የተሰባሰበው ኅቡዕ ማኅበር ውስጥ ቀሪ አባላትን ይዘው ቀጣዩን ስራ ለመስራት ወደፊት መጓዝ ጀመሩ፡፡

በዚህም መሠረት

፩ኛ አበበ ከበደ

፪ኛ ታደሠ መንግሥቱ

፫ኛ አቶ ሥዬም ወ/አብ

፬ኛ አቶ መኮንን ዋሴ* ነበሩ፡፡

*መኮንን ዋሴ የሚለው ስም መስፍን ዋሴ በሚል ታደሰ መንግስቱ ጠቅሰውታል ይሁንና ደጃዝማችም ሆኑ ደ/ር አክሊሉ መኮንን ዋሴ እያሉ በመጥራት ተጠቅመዋል፡፡ የአምስትኛውን እና ስድሰተኛውን ስም ማግኘት አልተቻለም ፡፡ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት በዚህኛው ውስጥ በአባልነት የለሁበትም ብለዋል፡፡

ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው ዜና ሕይወቱ ለብፁዕ አቡነ መልከጻዲቅ በሚል በአቀነባባሪነት በፃፉት መፅሃፍ አቡነ መልከ ጻዲቅ እንደገለጹት በምስካየ ኅዙናን ቤተክርስቲያን አካባቢ በመነኮሳት ቤት ፯ ወጣቶችን በግል እየሰበሰብኩኝ አስተምር ነበር ብለው ከላይ የተጠቀሱት ፬ ሰዎች ላይ ሞገስ ብሩክ እና ወይዘሪት የሺ እመቤት እማኙ የሚባሉ ሥሞችን በመጨመር የተምሮ ማስተማር ማኅበር እንዲመሠረት እንዳደረጉ ገልፀዋል፡፡

ይሁንና ከዚህ መፅሐፍ ውጪ እነዚህ ሁለት ተጨማሪ ሥሞችን ማግኘት አልተቻለም፡፡

የ፲፱፻፴፱ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያነሱትን የሃይማኖት ቅሰጣን ተቃውሞ ተከትሎ በ ፲፱፻፵ ዓ.ም ለሁለቱም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ማለትም ለተፈሪ መኮንንና ለእቴጌ መነን ( በአሁኑ አጠራር የካቲት ፲፪ ከፍተኛ ትምህርት ቤት) ተማሪዎች ሲባል በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ቤተ ክርስትያን መሰረት ተጣለ፡፡

የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አመሠራረት በሚለው መጽሓፍ አባ ተክለ ማርያምእንደገለጹትንጉሠነገሥት ቀ.ኃ፣ሥ መሠረት በተጣለበት ቀን ባደረጉት ንግግር “…በተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ክበብ ውስጥ ይህን የአዲሱን ቤተ ክርስትያን መሠረት ሥንመሠርት በዚህ ተማሪ ቤት የሚማሩ ክርስቲያናውያን ወጣቶች የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታቸውን ሥርዓት እንዲጠብቁበት ሥርዓተ ጸሎትና ሥርዓተ ቁርባን በመፈጸም እንዲጠቀሙበት አስበን ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ይኽም የም.ኅ.መ.ገ  ከነበረበት የቀድሞው ቀ.ኃ.ሥ በአሁኑ አጠራር የካቲት ፲፪ ሆስፒታል ወቶ አሁን ባለበት ቦታ እንዲሰራ ያደረገው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ና የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በዚህ ሥፍራ መገኘትና በኅቡዕ የተማሪዎች ማኅበር በወቅቱ የተነሳው ረብሻና ተቃውሞ ላይ ባነሡት ምክንያት መሆኑ ግልጽአድርጎታል ፡፡

ታቦተ መድኃኔዓለም

የመድኃኔዓለም ፅላት በ፲፰፻፺፭ ዓ.ም በግርማዊ ዳግማዊ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ትዕዛዝ በመምህር ፈቀደ እግዚእ ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰዶ ሲፀለይበት ቆይቷል፡፡

“ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ን.ነ.ዘ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ፲፱፻፵፫ ዓ.ም እንደጻፉት ንጉስ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስደት እንዳሉ ልመናቸውንና ፀሎታቸውን የሚያቀርቡበት በእምነታቸው ላይ ምግባራቸውን የሚያጠናክሩበት ቤተ ጸሎት ስለቸገራቸው አንድ ጽላት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ስላሰቡበት ወደ እየሩሳሌም ለእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ በጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም እንዲህ የሚል መልዕከት ላኩላቸው  “የእግዚአብሔርም ቸርነት ፈቅዶልንና አሰናብቶን ወደ እየሩሳሌም እስከምንመጣበት ቀን ድረስ የሃይማኖት ችግር እንዳያገኘን የሚያድጉትም ልጆች የሃይማኖታቸውን መሠረት እንዳያጡት አስበን አንድ ጽላትና አምስት መነኩሳት የሚያስፈልገውን ንዋየ ቅዱሳትና መጽሐፍ ሰጥተውት ይዞ እንዲመጣ አባ ሐናን ልኬዋለሁና ከመምህር ገሪማ ጋር ተማክራችሁ ዓቢይ ጾም ሳይገባ እንዲደርስ አድርጋችሁ እንድትልኩልን ይሁን ብለውበላኩላቸው መሠረት እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ድረስ በስደት ያለች የኢትጵያ ቤተክርስትያንእየተባለበሃገረ እንግሊዝ በስደት የሚገኙ ንጉሣውያን ቤተሰቦችና ለሌሎች ምዕመናን ለሥርዓተ አምልኮ መፈፀሚያ እንዲሆን በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ ከአምስት ልኡካን ጋር በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ሎንደን ሄዶ እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም እንግሊዝ ሀገር አገልግሎአል፡፡የመድኃኔዓለም ታቦት በነሐሴ ፲፫ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ግርማዊት እቴጌ መነን አዲስ አበባ በገቡበት ቀን አባ ኃይሌ ቡሩክ የተባሉት መነኩሴ ይዘውት ገብተዋል፡፡ ታቦቱም በቤተ መንግስት የተለየ ቦታ ተደርጎለት በአባ ኃይሌ ቡሩክ ጠባቂነትና አጣኝነት ከቆየ በኋሏ ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፭ ዓ.ም ተመልሶ ቀድሞ ቀ.ኃ.ሥ በዛሬው የካቲት ፲፪ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ምሥካየ  ኅዙናን በመባል ተሰይሞ ተተክሎ ነበር፡፡

የምሥካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም መነኮሳት በኅብረት ለመኖር /የአንድነት ኑሮ/ ለመኖር በመስማማታቸው በግንቦት ፲፮ ቀን ፲፱፻፴፯ ዓ.ም በብፁዕ እጬጌ ገብረጊዮርጊስ /በኃሏ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባሰልዮስና/ ሌሎች መምህራን ሊቃውንት በተገኙበት በዚሁ ስፍራ በቅዳሴ ተከብሯል፡፡

የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አዲስ ህንፃ ቤተክርስቲያንለመስራት በሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵ ዓ.ም በ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ የመሠረት ድንጋዩ ተጣለ የተጣለውም በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ክበብ ውስጥ ነው:: በዚህ ሥፍራም እንዲሠራ የሆነበት ምክንያት ለተፈሪ መኮንንና ለእቴጌ መነን ተማሪዎች ሲባል እንደሆነ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል ፡፡ መሰረት የተጣለበት ወቅትም የተማሪዎች የሃይማኖት ተቃውሞ በተደረገበት ዓመት መሆኑ ይህንኑ ያመለክታል ፡፡ የቤተክርስቲያኑ ሥራ በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም ሚያዚያ ፳፯ ቀን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀ.ኃ.ሥ. ግርማዊት እቴጌ መነንና ሌሎቹም በተገኙበት ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፡፡ የመጀመሪያውም አስተዳዳሪ አባ ሐና ጀማ ሆነው አገልግለዋል፡፡

አበበ ከበደ ና ጓደኞቻቸው ከተፈሪ መኮንን ት/ቤት ወጥተው በከፍተኛ ትምህርት ተመርቀው መደበኛ ሥራ ላይ እንደ ተሰማሩ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት የጠነሰሱትን የዚያን ጊዜውን ጥምረታቸውን እንደገና አጎልብተው የሚያስቡትን ለመፈጸም እንዲችሉ አመቺ ጊዜን በመጠበቅ በየጊዜው እየተሰባሰቡ ይወያዩ ነበር፡፡አባ ተክለማርያም በጻፉት የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አመሰራረት በሚለው መጽሓፋቸው አምስት ወይንም ስድሰት በመሆን ከ፲፱፻፴፯ ዓ፣ም ጀምሮ  በቤተክርስትያን ጥላ ስር ለመሆንና ማኅበር ለመመስረት ይጠይቁ ነበር ብለዋል፡፡

በም/ኅ/መ/ገዳም ጥላ ሥር ለመሰባሰብ ሲሞክሩ በዚያን ግዜ ንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ የገዳሙ የበላይ ጠባቂ ከነበሩት አባ ሀና ጅማ ከአስተዳዳሪው መምህር ተክለ ማርያም ያገኙትን ይሁንታና ድጋፍ መሠረት በማድረግ አቶ ገብረ ጊዮርጊስ አጋዤ የመሳሰሉትን እንዲሁም ተሥፋዬ ሙሉሸዋ ና ግርማቸው ብዙነህ ዘበንጉሥ ውሂብ መርጊያ ጎበናንና ሌሎች በስም ያልተጠቀሱትን ቀላቅለው ያዋቀሩት መድረክ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን ተምሮ ማስተማር ማኅበርን አስገኝቶ  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስትያን ጥላ ሥር ከተዋቀሩት ማኅበራትና ሰንበት ት/ቤቶች በዘላቂነት ረዥም ዕድሜ ለማስቆጠርየበቃ መንፈሳዊ ማኅበር ለመመሥረት በቅተዋል፡፡( የተምሮ ማስተማር ማኅበር አመሠራረት አጭር መግለጫ)

በተጨማሪም ሊቀሥልጣናት ሀብተማሪያም ወርቅነህንና (በኋላ አቡነ መልከጼዲቅ) በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በግብረገብ መምህርነት ተመድበው ሲያስተምሩ የነበሩትን አባ መዐዛ ቅዱሳንን (በኋላ አቡነ ናትናኤል) ጋር በመሆን በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም ከተፈሪ መኮንን እና ከእትጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር  የተምሮ ማስተማር ማኅበርየሚል ስያሜና መተዳደረያ ደንብ እንዲጸድቅለት አድርገዋል፡፡

ተምሮ ማሰተማር የሚለውን ስያሜ ያወጡት ገብረ ጊዮርጊሰ አጋዤ  እንደሆኑ ከቀሲስ ታደሰ መንግሥቱ ከመርጌታ ረታ አሳልፍና ከመምህር ታዬ አብርሃም እንዲሁም ከልጃቸው ሲ/ር የሺመቤት ገብረ ጊዮርጊስ ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል፡፡

 

የተምሮ ማሰተማር ማኅበር የሚለውን ስያሜ
 የተምሮ ማሰተማር ማኅበር የሚለውን ሲያሜ ያወጡት አቶ ገብረጊዮርጊስ አጋዤ ከማኅበሩ አባላት ጋር

    አቶ አበበ በተፈጥሮ የታደሉትን ችሎታና እውቀት በትምህርት ከቀሰሙት እውቀትና ሙያ ጋር በማዋሐድ በሃይማኖትና በቆራጥ የሥራ ወዳድነት እየታገሉ ለታረዙ ለተራቡ ለታመሙ ለደከሙና ረዳት ለሌላቸው ብርሃናቸውን ላጡና ዕጓለማውታ ወዘተ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሰው ታላቅ የግብረ ገብ ሰው እንደነበሩየህይወት ታሪካቸው ያስረዳል ፡፡አበበ ከበደ የተምሮ ማሰተማር በጎ አድራጎት የሚል ጽሕፈት ቤቱን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ያደረገ ድርጅትም መሥርተው ነበር(የተምሮ ማሰተማር ማኅበር ፋይል)

አቶ አበበ ከበደ በተፈሪ መኰንን ት/ቤት በነበሩበት ወቅት በሃይማኖታቸውና በግብረ ገብነታቸው በጓደኞቻቸው መሐል የታመኑና የተወደዱም ነበሩ፡፡ የተጣሉትን መምከርና በማስታረቅ የወንጌልቃል አንዲስፋፋ በመቀስቀስ ይሳተፉ ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ በት/ቤት በ፲፱፻፴፱ የተጀመረው የካቶሊክ ሚሲኖዊያን የሃይማኖት ቅሰጣን ለመከላከል የተጣሉትን ማስታረቅና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚል ሸፋን የተቋቋመው ማኅበርበአቶ አበበ ከበደ አሰተባባሪነትና መሪነት በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ ቅጽር ግቢ ውሰጥ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ ይኸው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሰንበት ትምህርት ማሰተማሪያ በመሆኑ በየእሁድ ጠዋት በቤተ ከርስቲያኑ ውስጥ በእቅድና በሥነ ሥርዓት የሚከናወን ሰፊ መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጥበትን ማኅበርን እንዲሆን በማስቻል መስርተዋል በኃላፊነትም መርተዋል፡፡

በ፲፱፻፵፱ ዓ/ም “ተምሮ ማስተማር ማኅበር” ተብሎ የተሰየመው ማኅበር አቶ አበበ እውቀታቸውን ገንዘባቸውንና ትርፍ ጊዜአቸውን መስዋዕት አድርገው በማደራጀታቸው እስከዛሬ ድረስ ዓላማውንሳይስትና ሳይፈልስ እንቅስቃሴው ሳይዳከምና ሳይታጎል እያደገ ብዙ ለሆኑ ወጣቶች ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ከመስጠቱ በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤቶች በጀማሪነቱና በዘላቂነቱ ቋሚ አርአያ ለመሆን በቅቷል፡፡

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መኩሪያ የነበሩት አቶ አበበ ከበደ ያበረከቱት አገልግሎት በዚህ ሳያበቃ የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ዘመናዊ አደረጀጀትና አመራር እንዲያገኝ አንዲሁም ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በገዳሙ ሥርም ዘመናዊ ት/ቤት ተመስርቶ አኩሪ ደረጃ ላይ እንዲደርስ መነሻውንና መድረሻውን ቀይሰው እንዲመሠረት በማድረግ የመመጀመሪያ የቦርድ አባልም በመሆን ከፍተኛ ድርሻና አስትዋጽዖ አበርክተዋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ ለቤተክርስትያን ና ለአባቶች ፍጹም ቅን ሰው ነበሩ፡፡አባ ተክለማሪያም ለደጃዝማች ወልደሰማዕት  እንደነገሯቸውና ለዚህ ጥናት አቅራቢ እነደነገሩት የም.ሥ.ኅ.መ ገዳም በገቢ እጥረት በተቸገረ ጊዜ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ ዘንድ ቀርበው ሁሉ አድባራትና ገዳማት መተዳደሪያመሬት ሲኖረው ምስካየ ኅዙናን ብቻ ለምን ሳይኖረው ቀረ መነኮሳቱ ችግር ላይ ናቸው ይረከቡኝ ባሉአቸው ወቅት ንጉሡም ሁሉም ይነጠቃል ይወስድበታል ይልቅ ገዳሙንከአበበ ከበደ ጋር ተማከሩና ራሱን እንዲችል አድርገው ብለው ትንቢት አዘል ንግግር ስለመለሱላቸው ከአበበ ከበደ ጋር ሲማክሩገዳሙ እስከዛሬ አበል የሚያገኝበትን የባንኮ ዲሮማ ህንጻን አክሲዮን እያገኘ እንዲጠቀም የሚያስችለውን መንገድ በመፍጠር ጠቃሚ ስራ አከናውነዋል፡፡በወቅቱ ገዳሙና መነኮሳቱ ከፍተኛ አድናቆትን  ያገኙበትን የስጋጃ ስራን ዕውን እንዲሆን ከሃሳብ ማመንጨት ጀምሮ በተግባር እንዲውል ያደረጉሰው ነበሩ፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ተክለማሪያም በእግራቸው ለሥራ ጉዳይ ሲሄዱ ተመልክተው ወዲያውኑ ገዳሙ እስከዛሬ እየተጠቀመበት የሚገኘውን ቮልስዋገን መኪና ከካምፓኒው እንዲገዛ ያደረጉም ቅን ሰው ነበሩ፡፡

አበበ ከበደ ህይወታቸውን ሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ መንፈሳዊ ስራ ላይ የነበሩ አገራቸውንና ቤተ ክርስትያናቸውን በቅንነት ያገለገሉ ባለ ራዕይና ውዳሴ ከንቱን የሚጠሉ ታላቅ ሰው ነበሩ ፡፡በዚሁ ቅን አገልግሎታቸውና ታታሪነታቸው ከፍ ላለ ኃላፊነት ስለአስመረጣቸው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት በሥራው ዋና ኃላፊ ሆነው ከየካቲት ፬ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ.ም ጀምሮ በብቃት ይወጡት እንደነበር ታውቋል (በሪሁን ከበደ፡ ፲፱፻፺፫፣ መርጌታረታ አሣልፍ)፡፡

ይህድርጅት በ፲፩ ቦርድ አባሎች

(ልዑል አልጋ ወራሽ ልዕልት ተናኜ ወርቅና ፓትሪያርያርኩን ጨምሮ የነበሩበት የነበረ ሲሆን አቶ አበበ ከበደ በኃላ ፊት እንዲመሩት ሲደረግ ሁለት ቦርድ የነበረውን ማለትም አንዱ የዲሬክተሮች ቦርድ ሁለተኛው የበላይ ጠባቂ ቦርድን በአንድ አጠቃለውና የዲሬክተሮች ቦርድ እንዲነሳተደርጐ ሁሉንም አጠቃለው እንዲሠሩት ተደርጓል፡፡ አበበ ከበደም ወደ ድርጅቱ ከመጡ ጀምሮ ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ ነበር (በሪሁን ከበደ ፲፱፻፺፫)፡፡

ይህንንም ከፍተኛ ኃላፊት ከተረከቡ በኋላ በድርጅቱ ሥር ይተዳደሩ የነበሩትን

ሀ/ በደብረ ሊባኖስ በሐረርጌ የሚገኙ የአረጋውያን መጦሪያ ቤቶች በተሻሻለ ሁኔታ እንዲያገለግሉና አንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡

ለ/  እናት አባት የሌላቸው ሕፃናት በልዩ ልዩ እንክብካቤ የሚያድጉባቸው ቤተ ሕፃናት እንዲያስፋፉ ወጣቶቹም በቀለምና በሙያ ትምህርት በተሻለ ሁኔታ እንዲማሩና እዲሰለጥኑ

ሐ/ ረዳትና ወገን የሌላቸው ደካሞች ጤናቸው የሚጠበቅበትና የሚታከሙባቸው ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች እንዲሻሻሉና እንዲስፋፉ፤

መ/ በተፈጥሮና በልዩ ልዩ እክል ምከንያት ብርሃናቸውን ያጡ  ዓይነ ስውራን በልዩ እንክብካቤ ተይዘው እውቀትና ከፍተኛ ሙያ  የሚገበዩባቸው ትምህርት ቤቶች ዘመናዊና ዘላቂነትባለው መንገድ እንዲደራጅና እንዲስፋፋ በማድረግ እጅግ ብዙ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መገልገያ እንዲሆኑ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በድርጅቱ ሥር ከነበሩት ከሕፃናት ማሳደጊያዎችና ከሰበታ መርሐ ዕውራን* ት/ቤት ጀምረው በልዩ ልዩ ሙያ ሠልጥነው ሀገራቸውንና ወገኖቻቸውን በብቃትና በኩራት ያገለገሉበርካታ ዜጎችን አፍርተዋል፡፡  በአሁኑ ወቀት በስፋት አልግሎት ከሚሰጡት የቅዱስ ጳውሎስ ሆሰፒታል ወ/ሮ በለጥሻቸው ክሊኒክ የአክሱም  ቅ/ማርያም ሆስፒታል ወዘተ ለአብነት ያህልየሚጠቀሱ በአቶ አበበ ከበደ አማካኝነት የተሠሩና የተደራጁ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ናቸው፡፡

*የዚህ ጥናት አቅራቢ ማረጋገጥ ባይችልም መርሐ ዕውር የሚለው ስያሜ ና ቃል በአጋጣሚ ይሁን ወይም በሌላ ከኣጼ ሱስንዮስ ካቶሊከመሆን ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው፡፡ ይኸውም መርሐ ዕውር ትምህርት በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ እራሱን የቻለ የቁጥር ትምህርት (የዘመን አቆጣጠር ስልት) ሲሆን በ፲፯ኛው ምዕት ዓመት ኣጼ ሱስንዮስ የካቶሊክ ዕምነትን ከተቀበሉ በኋላ መርሐ ዕውር መጽሓፍ እንዲጠፋ አዘው ነበር፡፡ዓቃቤ ሰዓት አቦሞ የሚባል ሊቅ መጽሐፉን ይዞ በረሓ በመሄድ እዚያ ትምህርቱን እያሰላሰለ ጊዜው እስኪያልፍ ድረስ ቆይቶ አጼ ፋሲለደስ ሲነግሥ ተመልሶ በመምጣት ትምህርቱን አሰፋፍቶታል፡፡(ስርግው ሀብለሥላሴ የአማርኛ የቤተክርስትያን መዝገበ ቃላት) ፡፡

በአገራችን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አካል ጉዳተኞች ብርሃናቸውን ያጡ ዓይነ ሥውራን ደካሞች ወዘተ በዘመናዊ ተቋም ተደራጅተውናተባብረው በአንድነት ሠርተው ሕይወታቸውን መምራትና ከሁሉም ጋር በእኩልነትና እየሰሩ መኖር እንደሚችሉ የታየበትና የተመሰከረበት በሃገራችን የመጀመሪያ ሃሳብ የነበረውን “የተዋህዶ ጥበብ የጃንጥላና የባትሪ ድንጋይ ፋብሪካ” በእሳቸው መሪነት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነበር፡፡ ይህም በአርአያነቱ የወጭ አገር አጥኚዎችን ሳይቀር የሚስብና የሚጎበኝ ድርጅት ነበር፡፡

እነዚህን በመሳሰሉ በጎ ሥሪዎች በመሳተፋቸውና በመደበኛው ሥራቸውም አኳያ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመታወቃቸው ጄኔቭ የሚገኘው የዓለም አብየተ ከርስቲያናትና ናይሮቢ ኬንያ ላለው የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤዎች ቋሚ የምክር ቤት አባል ሆነው በመመረጥ አገልግለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስትያን ኢንተር ቸርችኤይድ ኮሚቴ ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡እያንዳንዱ የመንግሥት ሠራተኛና ግብር ከፋይ አንድ ብር በወር በማዋጣት በመንገድ ላይ በልመና ላይ የተሰማሩ ሁሉ አምራች ዜጋ የሚሆኑበት ልመና የሚቀርበትን ኘሮጀክቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥናት አቅርበው እንደነበረምታውቋል (ታደሰ መንግሥቱ፲፱፻፺፮)፡፡

እኚህ ታላቅ ሰው በቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት ባለአደራዎች የሥሪ አስፈፃሚ መማክርት የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት እንደራሴ በመሆንም አገልግለዋል (በሪሁን ከበደ ፲፱፻፺፫)

አቶ አበበ ከበደ ለፈጸሙት በጎ ሥራዎችና ለአገራቸው ለሰጡት ሰፊ አገልግሎት የዳግማዊ ምኒልክ የመኰንን ደረጃና የኢትየጵያ የክብር ኮከብ የትላቅ መኰንን ኒሻኖች ተሸልመዋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ (ገብረ ኪዳን) ከወ/ሮ ጥሩወረቅ አስፋው(ወለተ ማርያም)ጋር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ደንብና ሥርዓት ሚያዚያ ፳ ቀን ፲፱፻፶፭ዓ.ም መ ም.ኅ.መ.ገ በተክሊል ተጋብተው ቆርበዋል፡፡ በፍቅርና በሰላም በመተጋገዝ በመረዳዳት መልካምየቤተሰብ መሪነታቸውን ከማስመስከራቸውም በላይ የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡

አቶ አበበ ከበደ ከዚህ ዓለም አልፈዋል፤ስለ ህልፈታቸው ምክንያት ግን ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡መረጌታ ረታ አሳልፍ በሰኔ ፳፪ ቀን ፲፱፻፰፮ ዓ.ም በደርግ መንግሰት ታስረው ባልታወቀ ስፍራ ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፸፩ ዓ.ም እንደተገደሉ ገልጸዋል ፡፡ ይህንኑ ሃሳብ ቀኑን ባይገልጹም ፐሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምም ጽፈውበታል፡፡በደርግ መንግሥት ከተገደሉ ና በተለምዶ ፰ ዎቹ በመባል የሚታወቁት በንጉሡ ጊዜ የነበሩ ከፍተኛ የሀገሪቱባለሥልጣኖች መታሰቢያ መጽሄት ላይ እንደተገለጸው ሐምሌ ፮፣ ፯ ወይንም8 በግፍና በራሥ ካሣ መኖሪያ ቤት በነበረውና በተለምዶ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ሰፈር አካባቢ በሚገኘው ግቢ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ መሆኑን ይገልጻል ፡፡

ለሞት የሚያበቃ ምን ክስ እንደነበረባቸው የዚህ ጥናት አቅራቢ  ለማየት ሞክሯል፡፡

አበበ ከበደ በሕይወት እያሉከሚናገሯቸው አንዱ ክርስትና እስከ ሞት ድረስ የሚጸኑበት ነው የሚል ነበር (መምህር ታዬ አብርሓም ፲፱፻፺፮)፡፡እኚህ በሕይወቴ ከያዝኩት እንደ በጎ አድራጎት ስራ ስክትክት የሚልልኝ የለም ብለው የሚያምኑት ቅን ሰው በደርጎች እጅ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ መገመት አያቅትም (ታደሰ መንግሥቱ ፲፱፻፺፮) ፡፡

የዚህ ጥናት አቅራቢ የተከሰሱበትን ለማወቅ ጥረት ሲያደርግ ያገኘውም መረጃ ሶስት ዓይነት ሆኗል ፡፡

ምስክርነት በባለ ሥልጣናቱ አንደበት በሚል ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ ግንቦት ፳፻፩ ባሳተሙት መጽሓፍ እንደገለጹት  የስድሳዎቹ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አሟሟት ውሳኔ አሰጣጥን አስመልክቶ በጊዜው በስብሳባ ለይ ተገኝተው ምርመራውን ያደረጉ ሰዎች (መንግሥቱ ገመቹ ወይንም በሻምበል ገብረየስ ወልደሃና እንደጻፉት የሚገመት) የደርግና የንዑስ ደርግ አባላት አሠራርን ያሳየ የልዩ ዐቃቢ ሕግ ፅሕፈት ቤት  ክስ ላይ ባቀረበው ሰነድ ፺፣፻ ከተሰኘው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በተራ ቁጥር ፳፫ ላይ የአበበ ከበደ ስም ተፅፎ የተሰጠው ምክንያትወይም ለሞት ያበቃቸው “አስቸጋሪ ነው” የሚል ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ በከንቱ ያለ ኃጢያታቸው ከግፈኞች ዕጅ መስዋዕትነትን ሊቀበሉየቻሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ሁለተኛው የቅርብ ጓደኛቸው የሆኑት ቀሲስ ታደሰ መንግሥቱ እንደሚገምቱትና እንደሚባለው ብለው እንደተናገሩት የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥትን ደርግ በሀሰት ከከሰሳቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ ፲፫ ቢሊዩን ዶላር በውጭ አገር ደብቀው አስቀምጠዋል የሚል ሲሆን አበበ ከበደም ለንጉሡ ቅርብ ስለነበሩ ና ለዓለም አብያተ ክርስትያናት ኅብረት ጽ/ቤት አገልግሎት እንዲሁም ለሚመሩት የቀ.ኃ.ሥ በጎ አድራጎት ድርጅትና ሌሎች ስራዎች ወደ ጄኔቭ ይመላለሱ ስለነበር የሚያውቁት ይኖራል በሚል ወይንም ገንዘብ በማሸሽ ተባብረዋል በሚልየሐሰት ክስ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል፡፡( ታደሰ መንግሥቱ ፣፲፱፻፺፮)

ይሁንና ይህንን ጉዳይ ማረጋገጥ ደርግ ራሱም አልቻለም ከዚሁ ክስ ጋር በንጉሡ ላይ ቀርቦ የነበረው ሌላው ምከንያት ወርቅ ደብቀዋል የሚል ሲሆን በጅሮንድ ገዛኸኝ ገብረ ማርያም ላይ ምርመራም ተደርጐ ነበር፡፡ ይህም ከአበበ ከበደ ጋር አብረው በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የመጀመሪያው በቦርድ ውስጥ ይሠሩ የነበሩት በጅሮንድ ገዛኸኝ ገብረ ማረያም በሰጡት ቃልና ደርግም ኅዳር ፫ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ.ም በአወጣው መግለጫ አንድም ወርቅ የጠፋ ወይንም የተሰወረ ነገር እንዳልነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ (በሪሁን ከበደ፤፲፱፻፺፫)፡፡

ሶስተኛው የትምህርት ቤት ጓደኛቸው ዶ/ር አክሊሉ ኃብቴ በቀጥታም ሳይሆን ከሰዎች እንደሰማሁት ብለው ለዚህ ጥናት  እንደገለጹት በንጉሠ ነገሥቱ በኩል ታማኝ ስለነበሩና ስራቸውንም በትጋት የሚሰሩ በመሆኑእርሳቸውም ፖለቲካውን እንዲቀበሉይፈልጉ የነበሩና ጥያቄውን ያልተቀበላቸው  ለአገሪቷ የሚጠቅማት ኮሚኒዝም ነው የሚሉ የግራ ፖለቲካ አራማጆች በጥላቻ ና በቂም በቀልገድለዋቸዋል ወይንም አስገድለዋቸዋልየሚል ነበር ፡፡አበበ ከበደ የእምነት ፀር የሆነውን ኮሚኒስትነትንይጠሉም እንደነበር ታውቋል፡፡

የሆነ ሆኖ እግዚአብሔር እንደፈቀደ እኚያ የተምሮ ማሰተማር አዳም እኚያ የሰንበት ትምህርትቤቶችመሥራች እኚያ ባለራዕይእኚያ  የነዳያን ረዳት ና ተስፋቸው የነበሩ ታላቅ ሠውሕይወታቸውበአሰቃቂ ሁኔታ በግፈኞች እጅ አልፏል፡፡

ለሀገርና ለወገን መገልገያ እንዲሆኑ ያነጹዋቸው ተቋሞች ግን ዘለዓለም ይኖራሉ፡፡ አቶ አበበ ከበደ እንደ አንድ ሻማ ሆነው በርተውና ተቃጥለው ጨለማውን ያስወገዱላቸው ማኅበራትም ለሌሎች የሚያበሩ የብርሃን ምንጮች ሆነዋል፡፡ በመልካም ሥራዎቻቸው ለዘለዓለም ሲታወሱ ሲመሰገኑና ሲከበሩ ይኖራሉ፡፡ይላል የሕይወት ታሪካቸው የተፃፈው መፅሔት፡፡

“…. መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤

ሩጫዬንም ፈጽሜያለሁ ሃይማኖቴንም

ጠብቄያለሁ እንግዲህስ እውነተኛ

ፈራጅ የሆነው ጌታ ያዘጋጀልኝን የጽድቅ

አክሊል ይሰጠኛል”

ከሶስቱ አባቶች ፩ አባ ሐና ጅማ

እንደ አቶ አርአያ ተገኝ ገለፃ አባ ሐናጅማ የተወለዱት ሚዳ ወረሞ በሚባል ስፍራ ነው፡፡ ትክክለኛ ስማቸውም አባ ገብረ ሐና ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ለማሳጠር አባ ሐና እያለ እንደሚጠራቸው የቤተክርስትያን መረጃዎች በሚል በዲ.ዳንዔል ክብረት የተፃፈው መፅሐፍ ይገልፃል፡፡ከበደ ተሰማ የታሪክ ማስታወሻ በሚለው መጽሃፋቸው ሺበሺ ጅማ በሚል መጀመሪያ ላይ ተጠቅመው በቅንፍ አባ ሐና ጂማ ብለው ጽፈዋል ፡፡ በሊቅነታቸውና በቀልዳቸው ከሚታወቁት አለቃ ገብረሐና ለመለየትም ሲባል ይሆናል አባ ሐና በሚባል አጭሩ ስማቸው የተጠሩት፡፡

አባ ሐና ጅማ ምንኩስናን የተቀበሉት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ነው በዚሁ ገዳምም በረድዕነት አገልግለዋል፡፡

ዐፄ ኃይለሥላሴ ሥልጣን እንደያዙ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአባቶች ቤተክርስትያን ለማሠራትና ለሀገራችንም ለቤተክርስቲያናችንም በአግባቡ እንዲውል የሚረዳን ያስፈልገናልናሰው ስጡን ብለውገዳሙን ቢጠይቁ ይህን ሥራ ከአባ ሐና በቀር ማንም አይሰራውም ተብለው የግምጃ ቤቱ ኃላፊ እንዳደረጓቸው ዲያቆን ዳንዔል ክብረት ገልጠዋል፡፡

በመንፈሳዊነታቸውና በትጋታቸው የሚታወቁት አባ ሐና ጠንካራ ሰራተኛችን በፍቅር ማሰራትን እንጂ በበላይነት ማዘዝን የማይወዱ እንደነበሩ አቶ አርአያ ለዲያቆን ዳንዔል እንደ ነገሩዋቸው በጥናታቸው ላይ ጽፈዋል፡፡

አባ ሐና የተምሮ ማስተማር ማኅበር እንዲጀመር አባላቱ እንዲበዙና ከንጉሠ ነገሥቱ ጀምሮ መኳንንቱና መሳፍንቱ አባል እንዲሆኑ በሀብት እንዲበለጽግ ታላቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡(ዲ.ዳንጌል ክብረት ፲፱፻፺፱).

አባ ሐና በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በግርማሜ ንዋይ እጅ በጥይት ረቡዕ ለኀሙስ ሌሊት ታህሳስ ፫ ቀን፣ ፲፱፻፶፫ ዓ.ም ተገድለዋል እሁድ ዕለትም በደብረ ሊባኖስ እንደ አቶ አርአያ ግምት በ፸ ዓመታቸው ተቀብረዋል፡፡ (ዲ.ዳንኤል ክብረት ፲፱፻፺፱).

አባ ሓና ጂማ ከታቦተ መድኃኔዓለም ና ከም.ኅ.መ.ገ ጋር የተለየ ታሪክ ያላቸው ገዳሙን የመጀመሪያ የበላይ ጠባቂ ሆነው ያሰተዳደሩ በስደት በእንግሊዝ ሃገር መንፈሳዊ አገልግሎት የሰጡ በተለይም የተፈሪ መኮንን ተማሪዎችን የመንፈስ አባት በመሆን ያገለገሉ አባት ነበሩ፡፡

የተምሮ ማስተማር ማኅበር መታሰቢያቸውን ሚያዚያ ፳፯፣፲፱፻፶፫ ዓ.ም ሲያደርግላቸው የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል (መዝ.፩፻፲፩) በሚል ርዕስ ባሳተመው ጽሑፍ የሕይወት ታሪካቸውንና የሰሩትን መልካም ፍሬዎችን ከዘረዘረበኋላ “እስከ መጨረሻው የታመንክ ሁን “ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን በመፈጸም ከጉድለትና ጥፋት ርቀው ቅን አገልግሎታቸውን ሳያቋርጡ በታህሣሥ ፯ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም የሞት ግዳጃቸውን በግፍ እንደ ተቀበሉና በገዳሙ ውስጥ ለተቋቋመው የተምሮ ማስተማር ማኅበር ሥራው የሚደረጅበትን እርምጃው የሚፋጠንበትን የሃብትና የጉልበት እንዲሁም የምክር እርዳታቸውን ያለማቁዋረጥ ያበረከቱለት እንደነበር፡፡ በመግለጽ እኒህን ታላቅ አባት በማጣቱ ማኅበሩንየሚሰማው ኀዘን እጅግ የመረረ ሆኖ ይገኛል በማለት ኀዘኑን በጽሑፍ አሥፍሮታል፡፡

አባ ሃና ጅማ (ፎቶ ከተምሮ ማስተማር ማኅበር)

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ታህሳስ ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም ባወጣው ጽሑፍ “በፖለቲካ ወይም በሥልጣን የአስተዳዳር ኃይል የሌላቸውን አባ ሐና ጂማን ገድለዋቸዋል፡፡ እኝህ ለወገኖቻቸው መንፈሳዊ ዕድገት የሚጥሩት የእግዚአብሔር ሰው በጾምና በጸሎት ዕድሜያቸውን ሙሉ የደከሙ ነበርሲል በመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ የተፈጸሙባቸውን ግድያ ገልጧል፡፡

  • ከሶስቱ አባቶች ታደሠ መንግሥቱ

የተምሮ ማሰተማር መቅረዝ “የፍቅር የትህትናና የጽናት አባት” ( ሥመ ክርስትና ንዋየ ማርያም)፡፡

ቀሲስ ታደሠ መንግስቱ የተምሮ ማስተማር ማህበር መቅረዝ፡፡ (ፎቶ ከተምሮ ማሰተማር ማኅበር)

ከአዲስ አበባ ሦሰት ኪሎ ሜትር እርቆ በሚገኘው እንጦጦ ማርያም አካባቢ በ ፲፱፻፲፰ ዓ.ም መጋቢት ፳፫ ቀን ነው የተወለዱት፡፡ አባታቸው መምህር መንግሥቱ ወ/ሚካኤል ይባላሉ፡፡ የእናታቸውም ስም ወ/ሮ አፀደ ነው፡፡ በስድሰት ዓመታቸው እናታቸው በአሥር ዓመታቸው ደግሞ አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን አሥራ ስድሰት ዓመት እስኪ ሆናቸው ድረስ እዛው እንጦጦ ኖሩ፡፡ በእንጦጦ እያሉም ውዳሴ ማርያም ጾመ ድጓ ተምረዋል፡፡ ከአቡነ አብርሃም እጅ ማዕረገ ዲቁናም በመቀበል በእንጦጦ ማርያም ቤ/ክ አልግለዋል፡፡ ቅኔ ለመማር ዝግጅት ላይ አያሉ አጎታቸው ወደ አዲስአበባ ይዘዋቸው ስለመጡ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት ለመከታተል ተገደዱ፡፡ እዚህም አዳሪ ት/ቤት እስኪ ገቡ ድረስ በመንበረ ልዑል ቅ/ማርቆስ ቤ/ክ ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ በሚያስቀድሱበትም ወቀት በድምጻቸው መልካምነት እየተመረጡ ይቀድሱ ነበር፡፡

በዘመናዊ ትምህርት በጣም ዕድለኛ ነኝ የሚሉት ታደሰ መንግሥቱ በትምህርት ብዙ እንዳልተቸገሩ ከ፩ኛ እስከ ፲፪ኛ ክፍል ድረስ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት እንደተማሩ ጊዜውም ከ09)#5 እስከ ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ለዘጠኝ ዓመታት እንደሆነ በወቅቱ ፲፪ኛ ክፍል ላይ የማትሪክ ፈተና ከእንግሊዘ እየመጣ እንዲፈተኑ ይደረግ ነበር በማለት ገልፀዋል፡፡ ያኔ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ ወደ ውጭ ሄዳችሁ ትማራላችሁ ተብለው በጣም ጉጉቱ አደሮባቸውም ነበር፡፡ ከሚወስዱት ሰባት ፈተናዎች ወስጥ አንድ እንኳን የወደቀ እንዲደግም ይደረግ ነበር (ሪፈር ይሉታል)፡፡ ከዚህ የተነሳ አንዳንድ ተማሪዎች በመውደቃቸው ምክንያት ተማሪዎች ሲያልፉ አንድ ላይ ነው የምትሄዱት ጠብቁተብለው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡

በመጨረሻ ደግሞ ዩኒሸርሲቲ ኮሌጅ ስለተከፈተ መጀመሪያ ሁለት ዓመት እዚህ ተምራችሁ ትሄዳላችሁ በመባላቸው ትምህርት ጀምረዋል፡፡ እርሳቸውም ከሌሎቹ ከፍያሉ (ትልቅ) ስለ ነበሩና እድሜአቸውም እየጨመረ ስለሄደ፣ሥራ ፈልገውገቡ፡፡ በስራ ላይ እያሉም በማታው መርሐ ግብር የሕግ ትምህርት ቀጥለው የነበረ ቢሆንም ሦሰት ዓመት ከተማሩ በኋላ ጤናቸው በመታወኩ መቀጠል አልቻሉም፡፡ በሌላ ጊዜም ሳይኮሎጂ ና ሶስዮሎጂ ትምህርት ጀምረው ስላልተመቸቻው ብዙም አልገፉበትም፡፡

በሥራም የሠሩበት መስሪያ ቤት በአንድ መሥሪያ ቤት ብቻነው፡፡ እሱም የግ.ቀ.ኃ. ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ጽ/ቤት እና የጸሕፈት ሚኒስቴር የሚባሉ መስሪያ ቤቶች (በአንድ ላይ የሚሠሩና አንድ ናቸው) ውስጥ በተርጓሚነት አገልግለዋል፡፡ በደርግ መንግሥት መሥሪያ ቤቱ ተዘግቶ በምትኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሲባል ለሰባት ዓመታት ሰርተዋል፡፡

ሥራ ሲጀምሩ ተርጓሚ ተብለው ገቡ ከዛም የክፍል ዳሬክተር ዋና ዳሬክተር በ ፲፱፻፶፬ ዓ.ም ገደማ ረዳት ሚኒስቴር ሆነውም ሠርተዋል፡፡ በ፲፱፻፸፫ ዓ.ም መጋቢት ፳፫ ቀን ልክ በ፶፭ ዓመታቸው ጡረታ ወጥተዋል ፡፡

የተምሮ ማሰተማር ማኅበርን ከመሠረቱት አባላት አንዱ የሆኑት ታደሠ መንግስቱ በ፲፱፻፴፱ዓ.ም የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ሳሉ የተጣሉትን ለማስታረቅ በሚል በኅቡዕ በተመሠረተው ማኅበር መስራች በመሆን ይሰባሰቡ እንደ ነበር ተናግረዋል፡፡ በዚያ ስብስብ ውስጥ ቀስ በቀስ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ይማማሩም ነበር፡፡ ይህም እያደገ ሄዶ በም/ኅ/መ/ገ እሑድ እሑድ በሦሰት ሰዓት ቤተክርስቲያኑ ተከፍቶላቸው ከእቴጌ መነን ተማሪዎች ጋር በመቀላቀል በአቡነ ናትናኤልና በአቶ አበበ ከበደ ከፍተኛ ጥረት በገብረ ጊዮርጊስ አጋዤ ስያሜ አውጪነት የተምሮ ማሰተማር ማኅበርን መተዳደሪያ ደንብ ተሰርቶለት በ፲፱፻፵፱ዓ.ም መሥርተዋል፡፡ አገልግሎቱን አስፍተዋል፡፡ አባልና መስራች የሆኑት በዚህ መልኩና ከዚያን ጊዜ ማለትም ከ፲፱፻፴፱ ጀምሮ ነው ማለት ነው፡፡ ቀሲሥ ታደሰ መንግሥቱ ከም.ኅ.መ. ገዳም ጋር የተዛመዱት ገና በልጅነታቸው ሲሆን፣ አሁን ያለው የገዳሙ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሲገነባ ምርጥ ምርጡን የመዓዘን ድንጋይ በማቀበል የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ሆነው እርሳቸውም ራሳቸው እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ የከበረ የተመረጠ የተወደደ ማዕዘን ሆነው ዘልቀዋል፡፡

ቀደም ባለው ዘመን በ፲፱፻፴፱ ና ፲፱፻፵ዎቹ በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ከመሰል የት/ቤቱ ባልደረቦቻቸው ጋር (የዛንጊዜዎቹ እነ አቶ አበበ ከበደ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት አቶሥዩም ወ/አብ አቶ መኮንን ዋሴና ሌሎችም ጋር በመሆን በት/ቤቱ ውስጥ ያጋጠማቸውን በኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታቸውና እምነታቸው ላይ ያንዣብብ የነበረውን ክስተት በመቋቋም ያከሸፉበት የኅብረት ክንዋኔ አቸው ጀምሮ ለሃይማኖታቸው በጽኑ ቆራጥነት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዚያን ወቅት ለነበረው እንቅስቃሴአቸው መሪ አርበኛው አቶ አበበ ከበደ እንደነበሩ ቀሲስ ታደሰ አረጋግጠዋል፡፡

ታደሠ መንግሥቱ ትሑትና ለመንፈሳዊ ስራ እልኸኛ ወስጡ እውነትን የተሞላ ግንደ ግሞ ሆደ ባሻና እንባ የሚቀናው ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ የሚጠላ ሰው ነበር ይላሉ የትምህርት ቤት ጓደኛቸው ደጃዝማች ወልደሰማዕትገብረወልድ፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ፈርቀዳጅ የሆነውን የተምሮ ማስተማር ማኅበር ከጥንስሱ ጀምሮ ከአቶ አበበ ከበደና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን መስርተዋል፡፡ በደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ አሳሳቢነት በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የነበረውን የጄስዊት ኢየሱሳውያን ካቶሊኮችን የቅሰጣ ስራ ተቃውመዋል፡፡ በመሩትም ተቃውሞ እንዲከሽፍ አድርገዋል፡፡ ከአቶ ገብረ ጊዮርጊስ አጋዤና ከሌሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ ውስጥ መሠረት በመጣል እጅግ ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ታደሰ መንግሥቱ የተምሮ ማስተማር ማኅበርን ከመመስረት አልፎ ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ ከአባልነት እስከ ማኅበሩ የበላይ ኃላፊነት ባሉት የሥራ ድርሻዎች እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በዚሁ ማኅበር ውስጥ ለተከታይ ትውልድና ለምዕመናን ጭምር አስተማሪና አርአያ በመሆን በየበዓላቱ ዛሬ መዘምራን የሚለብሱትን የማኅበሩ መለያ በመልበስ በመዘመር እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጥተዋል ፡፡ ታደሠ መንግሥቱ ማኅበሩ የጥምቀት በዓልን በጃንሜዳ ሲያከብር በዐውደ ምህረት በማስተማር በመዘመር በወቅቱ የተማረ ና ባለስልጣን ሆኖ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት እንደኋላ ቀር በሚቆጠርበት ዘመን አርአያ ሆነዋል፡፡ በተምሮ ማሰተማር“ ሰንበት ትምህርት” ቤት ከሰጡት ድካም ያልተለየው አገልግሎት በተጨማሪ የትህትና አስተማሪና አባት በመሆን የፈጣሪያቸውን ፈለግ ተከትለው ክርስትናን በቃል ሳይሆን በመኖር በሕይወታቸው ያስተማሩ አባት እንደሆኑ የተምሮ ማስተማር ማኅበር የረዥም ዘመናት ቋሚ ምስክራቸው ነው፡፡ ታደሠ መንግሥቱ ተምሮ ማስተማርን እንደ መቅረዝ ሆነው ብዙዎች ወጣቶችና ምዕመናን ብርሃናቸው እንዲበራ አድርገዋል፡፡ በህይወታቸው ሳሉ መመስገንን የማይፈልጉ ነበሩ፡፡

ትርጉም »