አንድ ሰው እና እባብ

ከዕለታት በአንድ ቀን አንድ እባብና አንድ ሰውዬ ከወንዝ ዳር በድንገት ይገናኛሉ፡፡ የተገናኙበት ምክንያት ሰውዬው ከወንዙ ማዶ ባለው መንደር ውስጥ ከሚኖሩት ዘመዶቹ መሀል አንዱ ሞቶ ስለነበር ለለቅሶ ወደዛው ለመሄድ ሲል ሲሆን እባቡም ደሞ ተወንዙ ባሻገር ወደ ሚገኘው ጫካ በመሄድ ምግቡን ለመፈለግ አስቦ ሲጋዝ ነበር አሁን ይገርምሻል ሁለቱም መንገዳቸውን ተያይዘው ወንዙ ጋ ይድረሱ እንጂ ወንዙን ተሻግሮ ለመሄድ ግን አስቸጋሪ ነገር ስለገጠማቸው በሀሳብ ተውጠው ያወጡና ያወርዱ ነበር፡፡ ይህም የገጠማቸው ችግር ምንድን ነው ብትይኝ እነሱ መንገድ በጀመሩበት ቀን ከወደላይ እጅግ በጣም ሀይለኛ ዝናብ ዘንቦ ስለነበር በዚህ የተነሳ ወንዙ እጅግ በጣም መሙላቱ ነበር እናም ሁለቱም ተሻግሮ ለማለፍ ቢሞክሩም ውሃው እጅግ የሚያስፈራና ለማለፍ የማይሞከር ስለሆነባቸው የግድ እስቲጎድል መጠበቅ ግድ ሆነባቸው፡፡ አሁን ከዚህ በኃላ ትዕግስታቸው እስኪያልቅ ድረስ ከጠበቁ በኃላ ወደየመጡበት ለመመለስ እያቅማሙ ሳለ ወንዙ ቀስ እያለ መጉደል ስለጀመረ ሰውየው ጓዙን ተሸከመና እንደምን በዋናም ቢሆን እየታገለ ለመሻገር ተነሳ በዚህ ጊዜ ይገርምሻል እባቡ ግን ጨርሶ ውሃ ካልጎደለ በስተቀር ለመሻገር ስለማይችል እንደዛ እስኪ ጎድልም ለመጠበቅ ደሞ በጣም ስለሚመሽበት ሰውየውን እያስተዛዘነ እባክህን ጌታው የማይችለው ጉልበት ያለው ማሻገር የተለመደ ነውና እባክህን እኔንም ካንተ ጋር አሻግረኝ የውሃው ግፊያ እንዳያስቸግረኝ በማለት አጥብቆ ለመነው ሰውየውም የእባቡ ሁኔታ ገርሞት እንዴ ምን ማለትህ ነው እንዴት አድርጌ ነው የማሻግርህ በማለት ቢጠይቀውእባቡም መልሶ አንተ መልካም ፈቃድህ ይሁን እንጂ እንዴት እንደምትሻገር መላውን እኔ እነግርሀለሁ አለው ሰውየውም እሺ በጄ መላው ምንድን ነው ቢለው ይኸውልህ ጌታው በጅህ እንዳትይዘኝ ትጠየፈኝ ይሆናል ኪስህም እንዳትከተኝ አታምነኝ ይሆናል ስለዚህ ሁለታችንም የሚያስማማን እንደሻሽ በጭንቅላትህ መጠምጠም ነው በማለት ተማፀነው አሁን ይገርምሻል ሰውየው ደግ ስለነበር እባብም በጣም አጥብቆ ስለተማፀነው በል እንዳል አለና በጭንቅላቱ ላይ እባብን ይዞ ውሃውን እየተጋፋ እንደምንም ታግሎ ወንዙን ተሸገሩ ከዛም ወደዳር ከወጣ በኃላ ወደ ጉዳዩ ለመገስገስ ጓዙን እያመቻቸ በል ከራሴ ላይ ውረድና ወደ ምትሄድበት ቀጥል እኔም ልሂድ ቢለው ለካ እባቡ ተንኳል አስቦ ኖሮ ራሱ ላይ ሆኖ እየተዝናና እንዴት ይመቻል እባክህ እዚህ ላይ ጉብ ብሎ መሄድ እናም አሁንም ለመውረድ ስላላሰኘኝ እዛ ወዲያ ጫካው ድረስ አድርሰኝ በማለት ጭራሽ ተደላድሎ ራሱ ላይ ቁጭ አለ አሁን ይገርምሻል በዚህ ጊዜ ሰውየውም በእባቡ ሁኔታ በጣም ተገርሞ እንዴት እንዴት ትላለህ ወንዙን አሻግረኝ ብለህ ለምነህኝ ስታበቃ መልሰሕ ያልተዋዋልነውን ሌላ መንገድ ተሸክመህ ውሰደኝ ትላለህ በማለት በሁኔታው በጣም አዝኖ በል አሁን ውረድ ቢለው እባቡም መልሶ ይቅል አትጨቅጭቀኝ ሰው ትወስደኝ እንደሆን ውሰደኝ እኔ እንደሆነ አልወርድም በማለት እምቢ አለው እንደውም ይገርምሻል ሰውየውን ያስፈራራው ጀመር አሁን ይገርምሻል በዚህ አጋጣሚ ቀበሮ በድንገት ስትመጣ ሰውየው ስላየ እንድትዳኛቸው ጠራትና ሁለቱም እሷጋር ቀርበው አቤቱታቸውን ያሰሙ ጀመር አሁን ሰውየው በመጀመሪያ ለቀበሮዋ ይኸው እግዚአብሄር ያሳይሽ ወንዙን አሻግረኝ ብሎ ሲያበቃ አሁን ደሞ ወዲያ ማዶ ታላደረስከኝ አልወርድም አለኝ በማለት አስረዳ እባቡም ደሞ በተራው ሲጠየቅ እኔ አልወርድም ያልኩት በሆነውም ቦታ ቢሆን እንዲህ የሚመች ስፍራ ስለማላገኝ ነው በማለት መለሰ አሁን ይገርምሻል እንዲህ እንዲህ እያሉ ከተከራከሩ በኃላ ቀበሮ የሁለቱንም አዳምጣ ስታበቃ እንግዲያው ፍርዱን ለመስጠት ሁለታችሁም ግራና ቀኝ መቆም ስላለባችሁ በል እባብ ውረድና በጀመሪያ በግራ በግራ በኩል ቁም አለችው እሱም እንደታዘዘው ወርዶ በመቆም ፍርዱን ሲጠባበቅ የእባብን ክፋት ቀበሮ በማወቅ ለትቢቱና ለክፋቱና ለተንኮሉ መቀጫ እንዲሆነው ብላ ሰውየውን እባብ ከግራህ በትሩ ከእጅህ እንግዲህ ሰውዬ ምኑን ልንገርህ ስትለው ሰውየውም የቀበሮ ቅኔ ስለገባው በያዘው ዱላ ራሱን ቀጥቅጦ አባረረው ይባላል፡፡
ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ

መልክቱ
– በሚያደርጉት ነገር መጠንቀቅ /ሰውየው/
– ጥሩ በሰራ ላይ ክፉ አለመስራት
– መጥፎ መስራት እንደማይገባ

ትርጉም »