እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። ማቴ 28፥19

አዘጋጅ የኅትመት እና ዝግጅት ስርጭት ክፍል

ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? (ማቴ. ፲፩፥፯)
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል እስከ ዐቢይ ፆም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዘመነ አስተርእዮ (የመገለጥ ዘመን) በመባል ይጠራል። መገለጥ የሚለው ቃል መታየት፣ መረዳት፣ ገሃድ መውጣት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ጌታችን መድኃኒታችን ከአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ መምጣቱን ይናፍቁ ለነበሩ ፍጥረታት በልደቱ መገለጥን ጀመረ። በልደቱ ቀን ከተገለጠው የተነሣ ሰው እና መላእክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና በምድርም ለሰው ልጅ ሰላም ሆነ” ብለው ዘመሩ። “ይህንን ምሥጢር እናይ ዘንድ ኑ እስከ ቤተልሔም እንሂድ” ሉቃ.፪፥፲፭ ብለው ሲናገሩ ከእረኞች አፍ መስማታችንስ ልደቱ ሊያዩት የሚገባ ምሥጢር መሆኑን የሚያሳይ አይደለምን? የሶርያው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ሲያጸናልን “ንዑ ርእዩ ዘንተ መንክረ፤ ይህን ድንቅ ምሥጢር ታዩ ዘንድ ኑ!” በማለት ምሥጢርነቱን በማወጅ ሕዝቡን ይጠራል፡፡
የአምላክ ሰው መሆን አንዱ ምክንያት ምሥጢረ መለኮት ለተሰወረበት ዓለም ምሥጢረ መለኮትን መግለጥ ነው፡፡ አዳም ሲፈጠር ከ፰ኛ የቅድስና መዐርግ ሆኖ ተፈጥሮ ምሥጢረ መለኮትን በማወቅ ይኖር ነበር፡፡ ክፉውን እና ደጉን ለይቶ ከሚያስታውቀው ዛፍ በመብላቱ የተነሣ ክፉ ዕውቀት ስለተጨመረበት ለነፍሱ ምሥጢረ መለኮትን ማወቅ ተሳነው። የሰውን ሐሳብ ከመታሰቡ አስቀድሞ የሚያውቅ ቅዱስ እግዚአብሔር የሰው ልጅ በደካማ ዕውቀቱ እና ደጋግሞ ጣዖታትን በማምለክ እንዳይጎዳ የአንድነት የሦስትነቱን ምሥጢር ሰወረ። ለዚህም አደል ቅድስት ኦሪት “እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” በማለት አጥብቃ አንድነቱን የምትሰብከው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ ግን ፶፭፻ (5500) ዘመን ተደብቆ የነበረው የቅድስት ሥላሴ የአንድነት እና የሦስትነት ምሥጢር ተገለጠ። አንድ እግዚአብሔር የምትል ቅድስት ኦሪት በአካል በስም ሦስት በመለኮት (በመመለክ) አንድ በሚል ማብራሪያ ይበልጥ ደመቀች።
እግዚአብሔር ሊገልጠው የፈለገውን ማንኛውንም ምሥጢር ሲገልጥ ሦስት ነገሮችን መምረጥ የሁልጊዜ ተግባሩ ነው፡፡ እነዚህም፦
ምሥጢሩን የሚገልጥበት ቦታ
ምሥጢሩን የሚገልጥበት ጊዜ
ምሥጢሩን የሚገልጥበት ሰው ናቸው፡፡
ዮርዳኖስን ለምሥጢር መግለጫ ቦታነት፤ ጥር ፲፩ን ለምሥጢር መገለጫ ቀንነት፤ ከቅዱሳን መካከል አምላኩን ለማጥመቅ የታደለው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ምሥጢር የሚገለጥበት ሰው አድርጎ መረጣቸው። ዘመኑ ዘመነ አስተርዕዮ (የመታየት ዘመን) ነውና አምላኩን ለማጥመቅ የታደለው መጥምቀ መለኮት ቅድስ ዮሐንስን ለመመልከት በዓይነ ልቦናችን ወደ ሚኖርበት ምድረ በዳ እንውጣ። “ቢጠፋብንስ?” ብላችሁ እንዳትሰጉ ይህን ቅዱስ የሚያሳየን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ቅዱስ አኗኗር፣ ሰለ አመጋገቡ፣ ስለ አለባበሱ በአጠቃላይ ስለ ሕይወቱ በስፋት ያሳየናል።
ዮሐንስ የምድረ በዳ ሰባኪ 
የቅዱስ ዮሐንስ የምድረ በዳ ኑሮ የሚጀምረው በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን እናቱ ሕፃኑን ከሄሮድስ ለማዳን ወደ ምድረ በዳ ይዛው በሸሸች ጊዜ ነው። በዚያም እናቱ በመሞቷ እናቱን ከአናብስት ጋር ቀብሮ ቶራ የምትባል እንስሳ ጡት እያጠባች አሳድጋዋለች። ቅዱስ ዮሐንስ ፴ ዓመት እስኪሞላው ድረስ የማስተማር ሥራን አልጀመረም ነበር። ዮሐንስ ፴ ዓመት ሲሞላው የስብከት አገልግሎቱን ጀመረ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ማ.ቴ ፫፥፩ “በዚያ ወራት መጥምቁ ዮሐንስ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች እና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ” በማለት የዮሐንስን የምድረ በዳ ሰባኪነት ይነግረናል። በምድረ በዳ እንጨት ሰባሪ ውኃ ቀጂ አይታጣምና ለነዚህ የመንግሥትን ወንጌል ይሰብክ ጀመር። ቅዱስ ዮሐንስ “ከተማ ካልደረስኩ ሕዝብ ካልበዛ አልሰብክም” የሚል ሰዋዊ ሐሳብ ያልነበረው ውዳሴ ከንቱን የሚጠላ ንጹሕ የእግዚአብሔር ሰው እንደሆነ ልብ ይሏል። “የይሁዳ ምድረ በዳ” የተባለ የአይሁድ ልቡና እንደሆነ አባቶቻችን መምህራን ተርጕመውልናል፤ እንዲህ በማለት “በምድረ በዳ የለመለመ ቅጠል የበቀለ ሣር እንደማይገኝ በአይሁድ ልቡናም የመልካም ነገር እንጥፍጣፊ አይገኝምና የአይሁድ ልቡና ምድረ በዳ ተባለ”። የዮሐንስ ስብከት ሰው የሚመጣውን ጸጋ ማለትም የጌታችን የመድኃኒታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን

ትምህርት ለመቀበል የተዘጋጀ እንዲሆን የማድረግ ዓላማ ያለው ነበር። መምህራን “ልብስ ለገላ ታጥቦ እንደሚዘጋጅ ዮሐንስም ሕዝቡን ለክርስቶስ ያዘጋጅ ነበር” ሲሉ የዮሐንስን ትምህርት እና ጥምቀት ይገልጹታል።
የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ
ቅድስ ዮሐንስ በሰባኪነት በምድረ በዳ ሲኖር ልብሱ የግመል ጠጉር ነበር፡፡ “ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው” ማቴ .፫፥፬፡፡ ግመል ጠጉር በብዛት የሌላት ግን በትንሹም ቢሆን ቢፈለግ የማይጠፋት ናት። ስንት በጠጉር የተሞሉ እንስሳት ሞልተው ዮሐንስ ምነው የግመል ጠጉር መልበሱ? ቢሉ “ዮሐንስ የሚታይ መምህር ነውና ልብሱም ያስተምራል” ይላሉ መምህራኑ። እንዴት አትሉም? በትምህርቱ “ሁለት ያለው አንዱን ለሌለው ይስጥ” እያለ ሲያስተምር የሚሰሙት ሁሉ “እሱ ምን አለበት የፈለገውን እንስሳ ገፎ እየለበሰ እኛ በብራችን የገዛነውን ልብስ ስጡ ይላል” እንዳይሉት ከነሱ የባሰ ምንም የሌለው ድሃ እንደሆነ ሲነግራቸው የጠጉር ድሃ የሆነችውን ግመልን መረጠ። መምህራኑ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ማብራራት ይቀጥላሉ፤ ግመል የሚገርም ተፈጥሮ ያላት እንስሳ ናት፡፡ አጥብቆ የመታትን ሰው እስከ ፯ ዓመት ድረስ አትረሳውም፤ ቦታ ጠብቃ እገደል አፋፍ ላይ ረግጣ ትጥለዋለች፤ ወይ ተፈጥሮ! የዮሐንስም ትምህርት “ንስሐ ግቡ” የሚል ነውና ሰው ይህን ትምህርት ሰምቶ ንስሐ ባይገባ በጌታችን በመድኃኒታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ባያምን፤ ጊዜን ጠብቆ በሞት ወደ ሲኦል፤ በዳግም ምጽአት ወደ ገሃነመ እሳት እግዚአብሔር እንደሚጥለው የሚያስተምር ነው። የኃጢአተኛውን መዳን እንጂ መሞት የማይፈልግ አምላክ በሰጠን ዕድሜ ንስሐ ልንገባ እንደሚገባን ልብ በሉ።

ሌላው መምህራን የግመልን ተፈጥሮ ሲነግሩን ቅድስት ኦሪት የሚበሉ እና የማይበሉ እንስሳትን ከፋፍላ ስታስተምር፤ ሰኮናቸው የተሰነጠቀ እና የሚያመሰኩ (የሚያመነዥጉ) እንስሳትን እንድንበላ ታዛለች ዘ.ዳ .፲፬፥፮። ግመል ሁለት ግብር አላት ታመሰኳለች በዚህ ልንበላት ስናስብ የእግር ጥፍሯ (ሰኮናዋ) ግን ድፍን በመሆኑ አንበላትም። ቅድስት ኦሪት ከአብርሃም ያልተወለዱ (አሕዛብ) ወደ ምኩራብ ዝር እንዳይሉ በምኩራብ ዘበኛ አቁማ “ኢይባእ አሞናዊ ወሞዓባዊ…አሞናዊ እና ሞዓባዊ እስከ ፲ኛ ትውልድ አይግባ” ዘ.ዳ .፳፫፥፫‐፬ እያለች ታውጅ ነበር። በዮሐንስ መንገድ ጠራጊነት በክርስቶስ የምትሠራ ወንጌል ግን “ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” ዮ.ሐ .፮፥፴፯ እንዳለ ጌታችን ሕዝብና አሕዛብን በአንድነት መንግሥተ ሰማያትን የምታወርስ ሕግ ናትና ይህን ለማመልከት የግመል ጠጉር ለበሰ። ልብ በሉ ምእመናን ወንጌል የዘር የጎሳ የቀለም ልዩነት የሌለባት ሁሉን በክርስቶስ አንድ የምታደርግ እራሷን የቻለች አንዲት መንግሥት ናት። ዘረኝነት ከዚች መንግሥት የሚያስነቅል አረምነት ነውና ራሳችንን ከዘረኝነት መጠበቅ ግድ ይለናል።
ዮሐንስ ጠፍር ይታጠቃል
ቅዱስ ዮሐንስ በወገቡ ላይ ጠፍር ይታጠቅ ነበር፡፡ “ወቅናቱ ዘአዲም ውስተ ሐቌሁ… በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር” ማቴ. ፫፥፬፡፡ ከዮሐንስ መታጠቂ ምን አለን? የሚልሰው እንዳይገኝ። በወንጌል የተጻፈልን ሁሉ የራሱ ትልቅ ዓላማ እንዳለው አንርሳ። መምህራን ስለ ጠፍር መታጠቂያው አስተማሪነት ይነግሩናል፤ እንዲህ ብለው “መጀመሪያ ጠፍርን ለመሥራት ከቆዳው ላይ የእንስሳው አካል ይነሣል፤ ከዚያም በውኃ ይነከራል፤ ያ የተነከረው ቆዳ ከውኃ ወጥቶ እንዲለፋ ይደረጋል፤ በመጨረሻም ቀለም ገብቶ መልክ ይይዛል” ይሉናል አባቶቻችን መምህራን፡፡ አቤት መታደል! ስንት አባት የሌለው ወፍ ዘራሽ በበዛበት በዚህ ጊዜ ከየት እንደመጣን ወደ የት እንደምንሄድ የሚነግሩ መምህራንን ያዘጋጀልን አምላክ ይክበር ይመስገን፡፡

በመንፈስ ቅዱስ የተመላችሁ መምህራን ሆይ የዚህስ ትርጉም ምን ይሆን? እንዲህ አሉ መምህራኑ “ቆዳው ከእንሳሳው አካል እንደተለየ በዚህ ዓለም እየኖረ ከዚህ ዓለም ግብር የተለየው ቅዱስ ዮሐንስ ወደሱ የመጡትን ሁሉ በስብከቱ ከኃጢአታቸው ይለያቸዋል። ቆዳው በውኃ እንደተነከረ በንስሐ ጥምቀት ያጠምቃቸዋል፡፡ በመጨረሻ የለፋው ቆዳ ወደ ቀለም መግባቱ በዮሐንስ ስብከት አምነው ጌታን ለተቀበሉት ሁሉ የልጅነት መልክ እና ጸጋ እንደሚሰጣቸው ሲናገር በወገቡ ላይ ጠፍር ታጠቀ።” ልብ በሉ ምእመናን በጥመቀት ልጅነትን ስላገኘን ብቻ ድኅነታችን ያበቃ እንዳይመስላችሁ፤ ልክ ከውኃ ወጥቶ እንደ ለፋው ቆዳ በምግባር በሃይማኖት ልንተጋ ይገባናል። በእውነት ምድረ በዳ ድረስ ወጥተው ሊያዩት የሚገባ መምህር ነው፤ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ።

መቼም በዓይነ ልቡና ወደ ምድረ በዳ ወጥቶ ይህን ሁሉ ለተመለከተ፤ በዓይነ ሥጋ ወደ ምድረ በዳ የሄደን ሰው “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ?” የሚለውን ጥያቄ ሲጠየቅ መስማቱ እጅግ እንደ ሚያስገርመው ግልጽ ነው። ለስም አጠራሩ ክብር እና ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዮሐንስ መናገር በጀመረ ጊዜ አይሁድን እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው ይለናል ቅዱስ ማቴዎስ “ጌታ ኢየሱስም ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ፡- ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸንበቆን?” ማቴ. ፲፩፥፯። ለምን የአይሁድ ወደ ምድረ በዳ የመውጣታቸው ምክንያት ጥያቄ ውስጥ ገባ?

የመጀመሪያው፡- በክርስቶስ ላይ ያሳዩት ተቃውሞ ነው። ወደ ዮሐንስ የሄደ ሰው ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት “ፍጡር” ሊለው ይችላል? ቅዱስ ዮሐንስ በሕይወቱም በትምህርቱም ስለ ክርስቶስ አምላክነት እየሰበከ ሕዝቡን ለክርስቶስ ያዘጋጅ የነበረ ነውና። ዮሐንስ ሲሰብክ “ከእኔ በኋላ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበር” ዮ.ሐ ፩፥፴ በማለት ምንም እንኳን በምድራዊ ልደቱ ጌታን በ፮ወር ቢቀድመውም እንደ አምላክነቱ ዘመን የማይቆጠርለት አምላክ መሆኑን ይመሰክራል።

በአንጻሩ ወደ ምድረ በዳ ዮሐንስን ለመመልከት የወጡት አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አብርሃም ቀኔን ያይዘንድ ተመኘ ደስም አለው” ቢላቸው “ገና ሃምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት” እሱም የአብርሃም ፈጣሪ ነውና “እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው”፡፡ ይህን ጊዜ ነው አይሁድ ዮሐንስ የመሰከረውን ምስክርነት፤ ያስተማረውን ትምህርት ትተው ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊወግሩት ድንጋይ ብድግ ያደረጉት ዮ.ሐ .፰፥፶፮‐፶፱።

ወደ ምድረ በዳ የወጡት አይሁድ ነፋስ ከሚወዘውዘው ሸንበቆ ውጭ ብፁዕ እና ጻድቅ መምህር መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ያዩት ይመስላችኋል? በዓይነ ሥጋ ቢያዩትም በዓይነ ሕሊና አላዩትም።

ሁለተኛው፡- አይሁድ የነበራቸው ምግባር ፍጹም ከዮሐንስ ትምህርት ጋር አለመጣጣሙ ነው። ዮሐንስ ስለ ፍቅር ደጋግሞ አስተምሯቸዋል፡፡ እነሱ ግን አሕዛቡ ጲላጦስ እስከ ሚታዘባቸው ድረስ በክርስቶስ ላይ እስከ ሞት ጨከኑ። ይገርማል! ዮሐንስን ያዩትና

ትምህርቱን የሰሙት አይሁድ አንድ አረማዊ ንጉሥ በክርስቶስ ላይ ያሳየውን ርኅራኄ እንኳን ማሳየት ተሳናቸው። “ጲላጦስም ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ” ማር. ፲፭፥፲፬። በእውነት አይሁድ ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ከነቢይም የሚበልጠውን ነቢይ እንዳላዩ አሁን በደምብ አስረዱን። አይ አይሁድ! የሚወዛወዝ ሸንበቆን ለማየት ምድረ በዳ ድረስ መድከማቸው ለምን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የማይሽረው የእግዚአብሔር ቃል ነውና የአንድ ዘመን ሰዎችን መክሮ ፣ታዝቦ ፣ገስፆ ብቻ አያልፍም፡፡ ጊዜ የማይሽረው የዘለዓለማዊው ንጉሥ የመድኃኔ ዓለም ቃል ዛሬም እኛን “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ?” ብሎ ይጠይቀናል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታቦታቱን ከየመንበረ ክብራቸው አንሥታ ልክ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ ወደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ እንደ ሄደ በማሰብ ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ትወርዳለች። በመሆኑም ታቦታቱን አጅበን ከቤታችን ወጥተን ወደ ባሕረ ጥምቀቱ እነሆ መጥተናል።

ካህናቱ በአለባበሳቸው መዘምራኑ በአዘማመራቸው ዛሬም እንደ ዮሐንስ ክርስቶስን ይሰብካሉ። “ኀዲጎ ፺ወ፱ተ ነገደ ቆመ ማእከለ ባሕር ገባ ወወጽዐ በሰላም… ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ በባሕር መካከል ቆመ ተጠመቀም” በማለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድና ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ የተስማሙበትን ቃል በመደነቅ ይዘምራሉ። እንዴት አያስደንቅ? ቅዱስ ጳውሎስ “የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም” ዕ.ብ .፪፥፮ እንዳለ የንጹሐኑን ያልበደሉትን የመላእክትን ዘር ትቶ፤ የበደለ የአዳምን ዘር በመያዝ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ከባሕር መካከል ቆሞ ሲታይ፤ ወደ ባሪያው አዳም መልክ እንደመጣ፤ ሊጠመቅ ወደ ባርያው ዮሐንስ ዘንድ መሄዱ ይህ ትሕትና እንዴት ያለ ትሕትና ነው? ሰውን ምንኛ እንደ ወደደው ታዩ ዘንድ ከመጣችሁ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ።

የዮሐንስን ስብከት ሰምታችሁ የንስሐን ፍሬ ለማፍራት የተዘጋጃችሁ ደግሞም ዮሐንስ “ነዋ በግዑ… እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ዮ.ሐ ፩፥፳፱ ብሎ ለዓለም ያስተዋወቀውን እውነተኛውን የክርስቶስን ሥጋውን ልትበሉ፤ እውነተኛውን ክቡር ደሙን ልትጠጡ ከመጣችሁ በእውነት እናንተ ከነቢይ የሚበልጠውን ጌታ ያገኙ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትን እንድርያስ እና ዮሐንስ ወንጌላዊን ትመስላላችሁ ዮ.ሐ .፩፥፴‐፴፱።

ነገር ግን ሥጋዊ አይናችን በሚያየው ነገር እየተሳብን ከሆነ በከተማ የሞላ ሸንበቆን ምድረ በዳ ድረስ ሄደው ካዩ አይሁድ በምን ተለየን? ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሁለመናዋ የምትሰብክ ሁና ሳለ ሥርዐቷን ወጓን ባህሏን ተመልክተን መማር ሲገባን በሥጋዊ ስሜታችን ብንመራ የአይሁድ ዕጣ እንደሚደርሰን ልብ በሉ። ዘፈን፣ ጭፈረ፣ ዝሙት ፣ ስካር፣ መዳራት እነዚህ ሁሉ በተቀደሰው ጥምቀተ ባሕር ቦታ ይዘው ሲታይ በእውነት አይሁድን በግብር እየመሰልናቸው ይሆን? ያሰኛል። የመጣንበትን ዓላማ ልናውቅ እና በዓመት አንድ ጊዜ ከሚገኘው በረከት ልንሳተፍ ይገባል።
ለዚህም እግዚአብሔር በቸርነቱ፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ፤ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በጸሎቱ፤ ቅዱሳን ሁሉ በረድኤታቸው አይለዩን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሀት ለእግዚአብሔር

ትርጉም »