ዘመነ  ክረምት በትምህርተ ወንጌል

አዘጋጅ ጌታቸው በቀለ

መግቢያ

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የዜማ ሊቃውንት የክረምት ወራትን በሰባት ንዑሳን ክፍላተ በመክፈል ለወቅቱና ለዕለታቱ የሚስማማ ምንባብ፣የሚዘመር መዝሙር በማዘጋጀት ከምእመናን ሕይወት ጋር በማዛመድ ከሰኔ 25-ሐምሌ 19 ቀን ድረስ ያሉትን 23 ዕለታት በአተ ክረምት/የክረምት መግቢያ/ በማለት ወንጌልን ያስተምራሉ፡፡
በዚህ የመግቢያ ወቅት በቅድስት ቤተክርስቲያን ዘርዕን፣ ደመናንና ዝናብን የሚያዘክሩ ምንባባት ይነበባሉ፤ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ ከመዝሙራቱም አንዱ፡-
“ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ይትፌሥሑ ነዳያን ይጸግቡ ርኁባን፤የዝናም ድምፅ ተሰማ ዝናም በዘነመ ጊዜ ችግረኞች ይደሰታሉ፤ረኀብተኞች ይጠግባሉ” /ድጓ/ የሚሉና “ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃል ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም” የሚሉና የመሳሰሉት ናቸው /መዝ146፣8/፡፡
የሚነበቡ ምንባባትም “በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናም የምትጠጣ መሬት ለሚያርሳትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለች እሾሁንና ኩርንችትን ግና ብታወጣ የተጣለች ናት፡፡ለመርገምም ትቀርባለች መጨረሻዋም መቃጠል ነው” የሚል ነው /ዕብ 6፣7-8/፡፡
********
ሊቃውንት ቤተክርስቲያን በአንድ ዓመት ውስጥ የሚገኙትን አራት ወቅቶች ከቅዱሳት መጻሕፍት ምስጢር ጋር በማስማማት ለየወቅቱና ለዕለታቱ የሚሆኑ ምንባባት፣መዝሙራት በማዘጋጀት ከኅብረተሰቡ ሥራና አኗኗር ጋር እንዲሁም ከወቅታዊው አየር ጠባይ ጋር በማ ያያዝ አራቱንም ወቅቶች በ91 ከ15 ኬክሮስ (አንድ አራተኛ) በመክፈል ለወቅቶቹም ስያሜ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ከእነዚህ ወቅቶች አንዱ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለው ዘመነ ክረምት ነው፡፡
እግዚአብሔር ክረምትን ሲያመጣና ዝናምን ሲያዘንም ከምናስተውላቸው ነገሮች አንዱ በመግቦቱ ከፍጥረቱ እንደልተለየ እንረዳለን፡፡እግዚአብሔር አምላክ ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምት፤ብርድና ሙቀት፤ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ቀንና ሰዓታት አማካኝነት ዑደታቸውን ጠብቀው እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም ሲሰጡ ይኖራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያውያን በአንድ ዓመት ውስጥ እየተፈራረቁ በሚመጡት አራት ወቅቶች የሚገባውን ወቅታዊ ሥራዎች እየሠሩ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ እንዳሉ ሁሉ ዘመነ ክረምት ሲመጣ የሚማረሩ አይጠፉም፡፡ለመሆኑ ዘመነ ክረምት ስንል ምን ማለታችን ነው? ከሌላው ወራቶች ምን የተለየ ነገር አለው?እግዚአብሐየር ይህን ዘመን የሰጠን ምን እንድናስተውል ነው? እነዚህንና ሌሎችም በኅሊናችን የሚጉላሉ ጥያቄዎችን እያነሣን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
ወርኀ ክረምት
መምህር ጥዑመ ልሳን “ያሬድና ዜማው” በሚለው መጽሐፋቸው የክረምትን ሥርወ ቃል ‘ከርመ፣ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ’ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ትርጓሜውም ወርኀ ዝናም፣ወርኀ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር ፣ዘመነ አፍላግ፣ዘመነ ጠል፣ዘመነ ደመና ፣ዘመነ መብረቅ… ማለት ነው፡፡
በዘመነ ክረምት ውኃው ይሠልጥናል፣አፈርን ያጥባል፣እሳትን ያጠፋል፡፡ ይሁን እንጂ በብሩህነቱ ከእሳት፣በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣በእርጥበቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር አብሮ ይኖራል፡፡ወርኀ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ፤ፍጡርን ከፈጣሪ፣መጋቢን ከተመጋቢ ለይቶ የሚሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡
ዘመነ ክረምት የዝናም፣ የዘርና የአረም ወቅት በመሆኑ ምድር በጠለ ዝናም ትረካለች ዕፅዋት፣አዝርዕትና አትክልት በቅለው ለምልመው የሚያድጉበት፤ምድር አረንጓዴ ለብሳ በሥነ ጽጌያት የምታሸበርቅበት ወቅት በመሆኑ ይህን ዘመን እንደ ቤተክርስቲያናችን ትምህርት በተለያዩ ነገሮች ይታወሳል፡፡ ወርኀ ክረምት፡-
የዘር ወቅት ነው፡-
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወርኀ ክረምት ስለዘር ጠቃሚነት በምሳሌ እንዳስተማረ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ከቁጥር 1 እስከ 18 ያለው ኃይለ ቃል ያስረዳል፡፡ ትምህርቱን ለመስማት ወደ እርሱ ለመጡት ሰዎችም በምሳሌ ሲያስተምራቸው “ዘሪ ሊዘራ ወጣ” ይላል፡፡ በምሳሌያዊ ትምህርቱ ዘሪ የተባለው እግዚአብሔር ሲሆን፣ዘሩ ደግሞ ቃለ እግዚአብሔር በእሾህ መካከልና በመልካም መሬት ላይ መውደቁን ገልጿል፡፡
በመንገድ ዳር የወደቀውን ዘር የሰማይ ወፎች መጥተው በሉት ይህም ቃሉን ሰምተው ለማያስተውሉ የልብ ዝንጉዓን ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ወፎችም የተባሉት አጋንንት ናቸው፡፡ ወፎች መጥተው በሉት ማለትም አጋንንት መጥተው አሳቱአቸው በሰሙት ቃል አልተጠቀሙም ማለት ነው፡፡
በጭንጫ ላይ የወደቀው ፈጥኖ ከበቀለ በኋላ ሥር የሚሰድበት አፈር ስላልነበረው ደረቀ፡፡ ይህም ቃሉን ለጊዜው በደስታ ተቀብለው መከራና ስደት በሚመጣ ጊዜ ግን የሚሰናከሉ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ጥልቅ ዕውቀት ስለሌላቸው ፈጥነው ሃይማኖታቸውን ይክዳሉ፡፡ በእሾህ መካከል የወደቀውም ዘር በቅለ፣አደገ፡፡ ፍሬ እንዲያፈራ እሾሁ አንቆ ይዞታል፡፡ ይህም እንደ ቃሉ እንዳይኖሩ በዚህ ዓለም ሐሳብና ባለጸግነት የሚያዙና የሚታለሉ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡
በመልካም መሬት የወደቀው ዘር ግን አንዱም ሠላሳ፣አንዱም ስድሳ ፣አንዱም መቶ ፍሬ አፈራ፡፡ ይህም ቃሉን ሰምተው ስለሚያስተውሉ በተግባርም ለሚገልጡት ሰዎች የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ቃሉን ሰምተው ሥራውን በሦስት ወገን ይሠሩታል፡፡ በወጣኒነት፣በማዕከላዊነትና በፍጹምነት፡፡ ክብሩንም በዚያው ይወርሱታል፡፡በወጣኒነት ሠላሳ ፣በማዕከላዊነት ስድሳ፣በፍጹምነት ደግሞ መቶ ፍሬ ያፈራሉ፡፡ ፍሬ የተባለው በሃይማኖት የሚፈጸም በጎ ተግባር ነው፡፡
ምድር ዝናምን ተቀብላ የዘሩባትን እንደምታበቅል ፣የተከሉባትን እንደምታጸድቅ ሁሉ የሰው ልጆችም በመምህራን አማካኝነት በልባቸው የተዘራውን፣በጆሮአቸው የሰሙትን ቃለ እግዚአብሔር በመልካም ሥራ አጉልተው ሠላሳ፣ስድሳ፣መቶ ፍሬ ማፍራት እንዳለባቸው የሚያስተምር ነው፡፡
የሥራ ወቅት ነው
ዘመነ ክረምት ለገበሬው የሥራ ወቅት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ በድካም ትበላለህ ምድርም እሾህና አሜኬላን ታበቅልብሃለች የምድርም ቡቃያ ትበላለህ ብሎ ባዘዘው መሠረት ገበሬው እሾሁን መንጥሮ ድንጋዩን ፈንቅሎ ወጥቶ ወርደ መሬቱን ያርሳል /ዘፍ 3፣17-19/፡፡ይህ ተግባርም በክረምት ወቅት ለበለጠ ሥራና ጥንካሬን የሚጠይቅ መሆኑን በግብርናው ሥራ የተጠመዱ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያንም “ዝናብ ለዘር ጠል ለመከር አታሳጣን” እያለች መሬት በወቅቱ ዝናብ እንድታገኝ ገበሬውም ዘሩን ዘርቶ አትክልቱን ኮትኩቶ በምድር በረከትን እንዲያገኝ ትጸልያለች፡፡ መሬት በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ በምትጠጣ ጊዜ ለሚያርሳት ደግሞ የሚጠቅም አትክልትን አብቅላ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና ተብሎ እንደተጻፈ/ዕብ 6፣7/፡፡
ገበሬውም ባለሰለሰው መሬት ላይ ዘሩን ከጎተራው እየዛቀ በማውጣት “ከወፍ አእላፍ አትርፈህ አብላን” እያለ ሳይጠራጠር በእምነት ይዘራል፡፡ እግዚአብሔርም የድካሙን ፍሬ ይሰጠዋል፡፡እንግዲህ ገበሬው የክረምቱን ቁር፣የበጋውን ሐሩር ሳይፈራ ከዘር እስከ መከር የደከመበትን የድካም ፍሬ አግኝቶ እንደሚደሰት፤እያንዳንዱም ክርስቲያን የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ታግሦ የሚደርሱበትን ፈተናዎች በመልካም ሥራና በትዕግሥት አሸንፎ የሕይወት ፍሬ በወቅቱ እንዲያፈራ በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን ታታሪውን ገበሬ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል፡፡
ዘመነ ክረምትና ምሳሌዎቹ
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሊቃውንቱ ዘመነ ክረምት በተለያዩ ነገሮች መስለው ምእመናኑን ያስተምራሉ፡፡እነዚህም፡-
ቃለ እግዚአብሔር
ወርኀ ክረምት የዝናም ወቅት በመሆኑ፤እግዚአብሔር ምድርን በዝናም እንደሚያረካ በጽጌ እንደሚያስጌጣት ሁሉ በዝናም የተመሰለው ቃለ እግዚአብሔርም የሰውን ልቡና ያረካል ለመልካም ሥራ እንዲነሣሣም ያደርገዋል፡፡ዝናምና በረዶ ከሰማይ ወርዶ ምድርን እንደሚያረካት እንድታበቅልና እንድታፈራ እንደሚያደርጋት “ዝናብና ከሰማይ እንደሚወርድ፣ምድርን እንደሚያረካት ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል” ይላል /ኢሳ 55፣10-11/፡፡
ዝናም ያላገኘ ተክል የሚፈለግበትን ፍሬ ሳያፈራ ቶሎ እንደሚደርቅ ሁሉ ከቃለ እግዚአብሔር የተለየ ክርስቲያንም ፍሬ ሃይማኖት ሳያፈራ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ደርቆ ጥሩ ሥራ ሰይሠራ ወደ ሲኦል ለመውደቅ ይደርሳል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ በመንፈሳዊው ሕይወቱ ለማደግ ቃለ እግዚአብሔር ዘወትር መመገብ እንዳለበት ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ፤በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት ገልጾታል /ማቴ 4፣4/፡፡
በወርኀ ክረምት ከምሳሌነቱ በተጨማሪ ልናስተውላቸው የሚገቡ በርካታ ምስጢሮችን ይዟል፡፡ ክፍለ ዘመኑ ዘር የሚዘራበት ነው፡፡ የተዘራው መልካም ዘር በመሬት ላይ ወድቆ በስብሶ ሳይቀር አድጎ፣አብቦና አፍርቶ በመከር ወራት ምርቱ ሲደርስ ገበሬውን ያስደስተዋል፡፡ ዘሩ በምድር ላይ ወድቆ እንዴት ለፍሬ እንደሚበቃ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም፣ይነሣልም እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ያድግማል፡፡ ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች” /ማር 4፣26-27/፡፡
አዝርዕቱ መዘራታቸው የሰው ልጆችን ሞት፣የተዘሩት በስብሰው ሳይቀሩ መብቀላቸው የሰው ልጆች በትንሣኤ የመነሣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ሰው በሕይወተ ሥጋ ሳለ አምሮበት፣ከብሮና፣በልጽጎ ከኖረ በኋላ በዚህ ዓለም የተወሰነለትን ጊዜ ጨርሶ ሲሞት በመቃብር ውስጥ ፈርሶና በስብሶ አይቀርም በትንሣኤ ሙታን ይነሣል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያው መልእክቱ ምዕራፍ 15 ቁጥር 37 ላይ “የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም… እግዚአብሔር ግን እንደወደደ አካልን ይሰጠዋል፤ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል”ይላል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሰማይ ዝናም ለዘር፣ጠል ለመከር እንዲሰጥ ምድርም የዘሩባትን እንድታበቅል፤ወንዞች ከመጠን አልፈው እንዳይሞሉና ጎርፍ አዝርዕትን ዕፅዋትን፣ሰዎችን፣እንስሳትን እንዳያጠፋ አዘውትራ ትጸልያለች፡፡በመጽሐፈ ቅዳሴ “በሚፈለግበት ቦታ እግዚአብሔር ዝናሙን ያዘንብ ዘንድ ስለ ዝናም እንማልዳለን፡፡ የወንዙን ውኃ ምላልን ብለን እግዚአብሔር እነርሱን እስከ ልካቸውና እስከ ወሰናቸው ይመላ ዘንድ ስለ ወንዝ ውእንማልዳለን፡፡ለዘርና ለመከር ሊሆን እግዚአብሔር ለምድር ፍሬዋን ይሰጣት ዘንድ ስለ ምድር ፍሬ እንማልዳለን” የሚል ነው፡፡ይህንንም ጸሎት ክርስቲያኖች ሁሉ ሊጸልዩት፣ሊማሩትና ሊያስተምሩት የሚገባ የወርኀ ክረምት ጸሎትና ትምህርት ነው፡፡
በቅዱስ ማርቆስ
በቤተክርስቲያናችን ትምህርት መሠረት ከአራቱ ወቅቶች አንዱ የሆነው ዘመነ ክረምት/ወርኀ ክረምት/ በቅዱስ ማርቆስ ይመሰላል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነውና፡፡ “በዚያ ወራትም ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡” እንዲል /ማር1፣7/፡፡ በዚህም የተነሣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ማርቆስን የውኃ ወቅት በሆነው በክረምት መስለውታል፡፡
ዕለተ ምጽአት
ዘመነ ክረምት በዕለተ ምጽአት ይመሰላል፡፡ክረምት አስፈሪና አስደንጋጭ የሆነ ነጎድጓድና ብልጭታ የሚበዛበት፤ሜዳውም የሚጨቀይበት ወቅት ነው፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 በቁጥር 20 ላይ “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” ሲል ስለ ክረምት ከባድነትና አስፈሪነት በቅዱስ ወንጌሉ ገልጾልናል፡፡ ክረምት ላዩ ውኃ፣ታቹ ውኃ ነውና ሰንበትም ለዕረፍት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ የሆነች ዕለተ ዕረፍት ናትና፡፡ አንድም በሰባተኛው ቀን በዕለተ ሰንበት አርፋለሁ ብሎ ስድስቱን ቀን በተገብሮ ይሰነብታል፡፡ በመሆኑም አርፍበታለሁ ባለበት ጊዜ ስደት እንዳይመጣበትና ከቀቢጸ ተስፋ እንዳይደርስ ይጸልይ ተብሏል፡፡ ይህ ለጊዜው ሲሆን፤ለፍጻሜው ግን በሃይማኖት ሳላችሁ ምግባር ሳትሠሩ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ፤እንዲሁም ዕለተ ምጽአት እንዳይደርስባችሁ ለምኑ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ወርኀ ክረምት ልምላሜ እንጂ ፍሬ የለውምና ሰንበትም ዕለተ ጽርዐት /ሥራ የማይሠራባት ዕለት/ናትና፡፡በመሆኑም ፍሬ ሳታፈሩ/ምግባር ሳትሠሩ/ በልምላሜ ብቻ ሳላችሁ /በሃይማኖት ብቻ ሳላችሁ/ እንዳትወሰዱ ለምኑ ሲል ነው፡፡ ከምግባር የተለየች እምነት ሙት ናትና ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው /ያዕ 2፣17/፡፡
ገበሬ በትዕግሥት የምድሩን ፍሬ ማግኘት እንደሚችል ሁሉ፤ክርስቲያኖችም እምነታቸውን አጽንተው በመያዝ የክርስቶስን መምጣት በትዕግሥት ከጠበቁ የማያልፈውንና የዘለዓለሙን ሕይወት የሚሰጠውን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ እንደሚችሉ ሲያስገነዝብ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሱ፡፡እነሆ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሰ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል” ይላል /ያዕ 5፣7/፡፡
ስለዚህ ፈጣሪያችን የሰጠንን ዘመነ ክረምት በጸጋ ተቀብለን ለሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት መሠረት የሆኑ ተግባራትን ተግተን መሥራት ይኖርብናል፡፡

ወስብሀት ለእግዚአብሔር

ትርጉም »