በዓለ ደብረ ታቦር

  ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 572 ሜትር ይሆናል፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ ምሳሌና ትንቢት ተነግሯል፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ “ታቦርና አርሞንኤም በስም ደስ ይላቸዋል” ብሎ የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን በዚህ ተራራ ላይ ገልጧል /መዝ. 88፥12/፡፡ በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሣራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነው፡፡ ምሳሌነቱም ባርቅ የጌታችን ሲሣራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ በአይሁድ እያደረ አምላክነቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን አጋንንት ድል የማድረጉ ምሳሌ ነው /መሳ. 4፥6/፡፡
   ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በቂሳርያ “የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ከጠየቃቸው ከስድስት ቀን በኋላ አዕማድ ተብለው የሚጠሩ ሦስቱን ሐዋርያት ይዞ ወደ ረጅም ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ ጌታችን ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፡፡ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱን ለሙሴ አንዱን ለኤልያስ በዚህ እንሥራ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ሐዋርያት ይህንን ሰምተው የጌታችንን መለኮታዊ ክብር አይተው በፊታቸው ወደቁ እጅግ ፈርተው ነበር፡፡ ጌታችንንም ተነሡ አትፍሩም አላቸው፡፡ በዚህ መልኩ አምላክነቱን ገለጠላቸው /ማቴ. 17፥1-10/፡፡

አዕማደ (የምስጢር) ሐዋርያት ለምን  ተመረጡ?

  አዕማደ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብን “አዕማድ ሐዋርያት” እያለ ጠርቷቸዋል /ገላ. 2፥9/፡፡ ስያሜውን ያገኙበት ዋናው ምክንያት የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ያስተባብሩ ስለነበረ ነው፡፡ ከዚህን በተጨማሪ ጌታችን በኢያኢሮስ ቤት ልጁን ሲፈውስ፣ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይና በደብረ ታቦር ምስጢረ መለኮቱን ሲገልጥ ከእሱ ስላልተለዩና ይዟቸው ስለሔደ ነው /ማር.5፥37-43/፡፡

  ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተመረጡበትን ምክንያት ሲያትቱ እንዲህ ብለዋል፡፡ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሹመት፣ ሽልማትና ክብር ፈላጊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሃሳብ እንዲወጡ ከብልየታቸው እንዲታደሱ ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለድኅነተ ዓለም የመጣው በሕማማቱ በሞቱ ቤዛ የሚሆነን አምላክ “ልሰቀል ነው” ባላቸው ጊዜ “አይሁንብህ” ብሎት ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ሃሳብ የጠላት እንጂ የሰው ልጆች ሊሆን አይችልም ከሞቱ በቀር ድኀነት ሊያስገኝልን የሚችል የለምና፡፡ ደቀ መዝሙሩ ግን ከሞተ ክብሬ ምንድን ነው ብሏልና “አይሁንብህ” አለ፡፡ /ማቴ. 16/ በሌላም ስፍራ እንዲሁ “ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲያስ ምን እናገኝ ይሆን?” በማለት ይጠይቃል፡፡ /ማቴ.19/፡፡ ጌታ ግን ዋጋችሁ ሰማያዊ ክብራችሁ ዘላለማዊ ነው ሲል እስከ ፍጹማን መዓርግ /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/ አድርሶ ብርሃነ መለኮትን ገልጦ ተስፋውን ነገራቸው፡፡

ሁለቱ ወንድማማች ደቀ መዛሙርትም እናታቸውን ልከው ሹመት ሽልማት መዓርግ ለምነዋል፡፡ ስለዚህም ጌታችን በደብረ ታቦር “በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ነገር” ስለሞቱ እንዲነጋገሩ አደረገ፡፡ ሞቱ እርግጥ ሆነ ማለት ነው፡፡ አባቱም “ኦሆ በልዎ ለክርስቶስ”፤ እሺ በሉት እርሱን ስሙት፡፡ ሞቱ እርግጥ በመሆኑ ከልባቸው እንዲጠፋ መርጦ ወደ ቅዱስ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡

“እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” እንዲል /ሚል 3፥6/ በእርሱ ዘንድ ወረት የለም፡፡ አስቀድሞ ከተዓምራቱ ከምሥጢሩ አይለያቸውም ነበርና ብርሃነ መለኮትን ለማየት አበቃቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ለማወቅ፣ ለመማር፣ ለመጠየቅ ያሳዩት ትጋት ምስጢር ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህ ምስጢር ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦ የሚቀር አይደለም፡፡ እስከ ዓለም ፍፃሜ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሲገለጥ፣ በመረጣቸውም ሲነገር የሚኖር ነው፡፡

ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ “አልክድህም አልተውህም”የሚለው /ማቴ. 26፥35/ ቢወድደው አይደለምን? ፍቅሩን መግለጡ ለክብር አብቅቶታል፡፡ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም “ጽዋዬን ልትጠጡ አትችሉም” ቢላቸውም /ማቴ. 20፥22/ አንዳችን በቀኝ ሌላችን በግራ ሆነን አብረንህ እንሞታለን ሲሉ በምስጢር ለምነዋል፡፡ ሞታቸውን ከሞቱ ጋር መደመራቸው ፍቅራቸውን መግለጣቸው ነው፡፡

ከተራራው ግርጌ

ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማንያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህ ማን ይኖራል” /መዝ.14፥1/ በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ “… በአንደበቱ የማይሸነግል፤በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ … በንፁሑላይ መማለጃን የማይቀበል ….” በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14፥1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረው ይሁዳን ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡

“የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ” የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል በጥበብ ይህን አደረገ፡፡ ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና” እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡

ምንጭ ሰማያት ቴሌቭዥን

ትርጉም »