በእምነታቸው ምሰሉአቸው

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

`በእምነታቸው ምሰሉአቸው`
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” (ዕብራ. 13፡7) ባለው መሠረት እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን የአባቶቻችንን የሐዋርያትን እምነት በመምሰል እነርሱ እንደጾሙት የእመቤታችን የፍልሰትዋን መታሰቢያ በየዓመቱ እንጾማለን፡፡


ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በዕለተ እሑድ ጥር 21 ቀን ከዚህ ዓለም በተለየች ጊዜ፣ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እናቱን እንዲቀብሩ ከየአገረ ስበከታቸው በደመና ጠቅሶ ሲሰበስባቸው፡፡ በክብር ገንዘው ካበቁ በኋላ፣ ሥጋዋን በጌቴሴማኒ የመቃብር ቦታ ለማሳረፍ ይዘዋት ሄዱ፡፡
ለምቀኝነት የማያርፉ አይሁድ ግን “ልጇን ሞተ፣ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ እያወኩን አሉ፤ አሁን ደግሞ እናቱን ሞተች ተነሣች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን?” በማለት ጉልበት ያላቸውን በመምረጥ ቅዱስ ሥጋዋን እንዲያቃጥሉት ላኩባቸው፡፡ ከተላኩትም መካከል “ታውፋንያ” የተባለው ቀድሞ ደርሶ የአልጋውን ሸንኮር በመያዝ ከመሬት ሊጥላት ሲሞክር መልአከ እግዚአብሔር ሁለት እጆቹን ቆረጠበት፡፡
እጆቹ ከዚያው ከአልጋው ላይ ተንጠልጥሎ ሳለ ጮኸ አለቀሰ፡፡ በዚህን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ በጸሎቱ እና በድንግል ማርያም አማላጅነት የእጆቹን ቸብቸቦ አንሥቶ ወደ ክንዱ ቢመልሰው ደህና ሆነለት፡፡ ይህም ሰው ባደረገው ነገር ተጸጸተና ተመለሰ፡፡ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ያዘዘው መልአክ የእመቤታችንን ሥጋዋን ነጥቆ፣ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወደ ገነት ዐሳረገው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ወደ ምድር ተመልሶ አይዞአችሁ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ በገነት ዕጸ ሕይወት ዛፍ ሥር ተቀምጦ አይቼ መጥቻለሁ አላቸው፡፡

እመቤታችን ያረፈችው በ64 ዓመቱ ሲሆን ይህም፡-
በእናት አባቷ ቤት – 3 ዓመት፣
በቤተ መቅደስ – 12 ዓመት፣
ጌታችንን ከወለደችበት ጊዜ አንሥቶ ከተወዳጅ ልጇ ጋር – ለ33 ዓመት ከ3 ወር፣
ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር – ለ15 ዓመት ከ9 ወር፣
ይህ ሲደመርም እስከ ጥር 21 ቀን እሑድ ዕለት ድረስ በዚህ ምድር – 64 ዓመት ኖሯ ዐርፋለች፤

ቅዱስ ያሬድ የእመቤታችንን ፍልሰተ ሥጋ አስመልክቶ ዝማሬ በተባለው ድርሰቱ “መላእክትና ሊቃነ መላእክት ቅዱስ ሥጋዋን ለማሳረግ በታላቅ ምስጋና ከሰማይ ወረዱ፤ አባቷ ዳዊት ከመሰንቆው ጋር ሙሴም የአገልግሎት ልብሱን ለብሶ፣ ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስም ወደ እርሷ መጡ ሥጋዋንም በወርቅ ማዕጠንት አጠኑ፡፡ ሱራፌልና ኪሩቤልም በላይዋ ክንፎቻቸውን ዘረጉ /ጋረዱ/፡፡ ከሰማያት ብርሃን የምስጋና መብረቅም ከደመናት ውስጥ ወጣ፡፡ ከምድር ወደ ሰማያት በምስጋና ከፍ ከፍ አለች ከልጇ ጋርም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” ብሏል፡፡ የዚህ ምሥጢር አባቷ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፡፡” (መዝ 44፡9) ያለውን የሚያዘክር ነው፡፡

ንጉሥ ሰሎሞንም “ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ” (መኃ 2፥10) እዚህ ላይ በትንቢት እመቤታችንን “ውበቴ” የሚላት ንጽሕናዋን ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር በሙሉ በሰይጣን ባርነት ተይዞ በጨለማ በነበረበት ጊዜ ብርሃን ክርስቶስን ያስገኘች የፀሐይ መውጫ በመሆኗ እመቤታችን በውስጥ፣ በአፍአ፣ በነቢብ፣ በገቢር፣ በሐልዮ ፍጹም ነቅዕ የሌለባት ድንጋሌ ሥጋ ድንጋሌ ነፍስ ድንጋሌ ኅሊና የተባበሩላት በነፍስ በሥጋ በልቡና ንጽሕት ቅድስት ልዩ በመሆኗ “ውበቴ” ይላታል፡፡
በአጠቃላይ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋዋ በክብር በእጸ ሕይወት ስር ማኑሩን ወልደ ነጎድጓድ ዮሐንስ ለሐዋርያት በነገራቸው መሠረት በዓመቱ ነሐሴ አንድ ጀምሮ ሁለት ሱባኤ እንደሚጾሙ ተቀጣጥረው ወደየአገረ ስብከታቸው የሄዱት ሐዋርያት በዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን እስከ ነሐሴ 14 ቀን በሚጾሙበት ወቅት ልጅዋ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋዋን አምጥቶ መሐላቸው አኑሮላቸዋል፡፡ ጌቴሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ በክብር ቀብረዋታል፡፡
በኋላም “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስ ታቦት” (መዝ.131፥8) ተብሎ በተነገረላት ተስፋ ትንሣኤና ትንቢት መሠረት እርሷም እንደ ልጇ ወደ መቃብር በወረደች በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን በልጇ ፈቃድ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ዐርጋለች፡፡
እኛም ይህንን ለማስታወስ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያትን በእምነት እና በምግባር ለመምሰል እነርሱ የጾሙትን ቀናት በማስታወስ ከነሐሴ 1 ጀምረን እስከ 15 ቀን ድረስ በየዓመቱ እየጾምን በነሐሴ 16 በዓለ ትንሣኤዋን እናከብራለን፡፡
ኦርቶዶክሳውያንን ሁሉ እንኳን ለጾመ ፍልሰታ አደረሳችሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በሚሰጠን ጸጋ ጾሙን በንጽሕና ጾመን ከእናቱ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት እንዲያሳትፈን እንመኛለን፡፡ አሜን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣
ወለወላዲቱ ድንግል፣
ወለመስቀሉ ክቡር!!

ትርጉም »