ታቦተ ቅድስት ድንግል ማርያምታቦተ መድኃኔ ዓለምታቦተ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ

ታቦተ መድኃኔ ዓለም

የመድኃኔ ዓለም ጽላት በ፲፰፻፺፭ዓ.ም. በግርማዊ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ ትእዛዝ በመምህር ፈቀደ እግዚእ አማካኝነት ወደ ኢየሩሳሌም ተወስዶ በዴር ሡልጣን (የንጉሥ ገዳም) ውስጥ ለ፴፬ ዓመታት ሲጸለይበት ቆይቷል፡፡ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ በስደት እንዳሉ ልመናቸውን እና ጸሎታቸውን የሚያቀርቡበት አንድ ጽላት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ስለአመኑበት ወደ ኢየሩሳሌም ለዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ (በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ) በጥር ፲፫/፲፱፻፳፱ ዓ.ም. “…አንድ ጽላትና አምስት መነኵሳት የሚያስፈልገውን ይዞ እንዲመጣ አባ ሐናን ልኬዋለሁና ከመምህር ገሪማ ጋር ተማክራችሁ ዐቢይ ጾም ሳይገባ እንዲደርስ አድርጋችሁ እንድትልኩልን ይሁን” ብለው በላኩላቸው መሠረት በሀገረ እንግሊዝ በስደት የሚገኙ ንጉሣውያን ቤተሰቦች እና ለሌሎች ምእመናን ለሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ከአምስት ልዑካን ጋር ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ለንደን ሄዶ እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. በእንግሊዝ ሀገር ቆይቷል፡፡

የመድኀኔ ዓለም ታቦት በነሐሴ ፳፫ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ግርማዊት እቴጌ መነን ዐዲስ አበባ በገቡበት ቀን አባ ኃይሌ ቡሩክ የተባሉት መነኵሴ ይዘውት ገብተዋል፡፡ ታቦቱም በቤተ መንግሥት የተለየ ቦታ ተደርጎለት በአባ ኃይሌ ቡሩክ ጠባቂነትና አጣኝነት ከቆየ በኋላ ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. ደግሞ ቀድሞ ቤተ ሳይዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል በዛሬው የካቲት ፲፪ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ምስካየ ኅዙናን በመባል ተሰይሞ ተተክሎ ነበር፡፡

የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም መነኵሳት በኅብረት /የአንድነት ኑሮ/ ለመኖር በመስማማታቸው በግንቦት ፲፮ ቀን በ፲፱፻፴፯ ዓ.ም. በዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ /በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ/ እና መምህራን ሊቃውንት በተገኙበት በቀድሞው ሥፍራ በቅዳሴ ተከብሯል፡፡

ታቦቱ ዐዲስ አበባ ከገባ ከሰባት ዓመታት በኋላ

የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ዐዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት በሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵ ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመሠረት ድንጋዩ ተጣለ፡፡ የተጣለውም በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ክበብ ውስጥ ነው:: በዚህ ሥፍራም እንዲሠራ የሆነበት ምክንያት ለተፈሪ መኮንን (ወንድ ተማሪዎች) እና ለእቴጌ መነን(ሴት ተማሪዎች) ተማሪዎች ሲባል እንደሆነ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ተጠናቅቆ በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. ሚያዚያ ፳፯ ቀን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀ.ኃ.ሥ. ግርማዊት እቴጌ መነን እና ሌሎቹም በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፡፡

በዚህ ወቅት ሥርዐተ ቅዳሴውን ያካሄዱት ልዑካን፤ ሠራኤ ካህን፡- ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ የሸዋ ጳጳስ፣ ተራዳኢ ካህን፡- ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የሲዳሞ ጳጳስ፣ ሠራኢ ዲያቆን፡- አባ ተክለ ማርያም (ኹለተኛ አስተዳዳሪ የነበሩት)፣ ተራዳኢ ዲያቆን፡- አባ ሐና ጅማ (የመጀመሪያ አስተዳዳሪ)፣ አባ ኃ/ኢየሱስ፣ አባ ገ/ሚካኤል ነበሩ፡፡

የገዳሙ ልዩ አስተዳደራዊ መዋቅር፡-
ገዳሙ የሚተዳደረው ቀጥታ በቅዱስነታቸው ትእዛዝ ነው፡፡ በሊቀ ጳጳስ የሚመራ አስተዳዳር ቦርድ አለው፡፡ የገዳሙ መምህር (አስተዳዳሪ) የሚመሩት የአስተዳደር ጉባኤ አለ፡፡ ከዚሁም ጋር መጋቢ፣ ቄሰ ገበዝ እና ሊቀ ዲያቆናት የየራሳቸው ሐላፊነት አላቸው፡፡

የመጀመሪያውም አስተዳዳሪ አባ ሐና ጅማ ሆነው በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. ግርግር እስከ ተገደሉበት ቀን ድረስ እንደሚገባ አገልግለዋል፡፡

ስያሜው እና ልዩ ሥርዐቱ

ከቤተ ሳይዳ ጀምሮ የገዳሙ ስያሜ ምስካየ ኅዙናን ማለት ያዘኑ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ይኽም ከላይ እንዳየነው የኢትዮጵያን አንባ አብሶአልና ያዘኑ ምእመናን እየመጡ እንባቸው እንዲታበስ በማመን የተሰየመ ስም ነው፡፡

ልዩ ሥርዓቱ በስሙ ትርጓሜ መሠረት ቤተ ክርስቲያኑ ከበሮ የማይመታበት ጸናጽልም የማይሰማበት ነገር ግን ሥርዐተ ቅዳሴ

                    ክቡር አባ ሐና ጅማ

የሰዓታት ጸሎት፣ የኪዳን ጸሎት፣ የሠርክ ጸሎት የንስሐ መዝሙር የሚቀርብበት የኅዙናን መጠጊያ ነው፡፡

የገዳሙ መምህራን /ብዛት

ከክቡር አባ ሐና እስከ አሁኑ መምህር ክቡር አባ ፍቅረ ማርያም ተ/ማርያም /ቆሞስ/ ድረስ ሃያ አንድ አበው አስተዳድረውታል፡፡

አበርክቶ

ገዳሙ ለተምሮ ማስተማር እጅግ ብዙ አበርክቶ ያለው ሲሆን፣ ጥቂቱን ለመግለጽ ያህል፣ እስከ ሰባዎቹ መጀመሪያ ድረስ እሑድ እሑድ የሚሰበሰብ ሙዳየ ምጽዋት ለተምሮ ማስተማር እንዲሰጥ አድርጎ ቆይቷል፡፡

የተምሮ ማስተማር ሰ/ት/ቤት የአገልግሎት ክፍሎች በወቅቱ በሃያ ስድስት ሺህ ብር ሲገነቡ ገዳሙ የራሱን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ አባቶች መነኮሳት በየጊዜው በሰ/ት/ቤቱ ጉባኤ በመገኘት፤ በመባረክ፣ በማስተማር፣ በመወያየት፣ ጽሑፎችን በማረም እና ልዩ ልዩ ሥራዎችን ከአባላቱ ጋር አብሮ በመሥራት ከተጀመረ ጀምሮ እስከ አሁን ታላቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ምክትል አስተዳዳሪ መጋቤ ኅሩያን አባ ኤልያስ በልሁ፣ ለተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት የበላይ ሰብሳቢ ሆነው ከአሥራ አንድ ዓመታት በላይ የሚደንቅ አገልግሎት እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

ተምሮ ማስተማር ለገዳሙ ትምህርቱ ቤቱ እንዲገነባ ሐሳብ በማፍለቅ እና ሙያዊ እገዛ በማድረግ፤ አባቶች በሚያዙት ሁሉ እየታዘዘ የልጅነት ግዴታውን እየተወጣ ከመገኘትም አልፎ ለገዳሙ አባቶች መነኰሳት እና ዲያቆናት የኮምፒውተር እና የምልክት ቋንቋ ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጎአል፡፡ በቅርቡ አባላቱን አስተባብሮ፣ መክስተ ፊደል ወሥዕል /ስክሪን/ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በመትከል ምእመናን ቅዳሴን በግእዝ እና በአማርኛ እንዲሁም ለውጪ ዜጎች እንዲያገለግል በእንግሊዝኛ ቋንቋ አዘጋጅቶ እሑድ እሑድ እያቀረበ ይገኛል፡፡

የምእመናን ድርሻ

ምእመናን ለነፍሳቸው ሲሉ፣ በቤተ ክርስቲያን እየተገኙ፣ የቤተ ክርስቲያንን በትምህርት እና በጸሎት አገልግሎቶች መሳተፍ ይገባቸዋል፡፡ ክርስቲያኖች ከአሥራት በኵራት ጀምሮ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በሐሳብ፣ በገንዘብ እና በጊዜም ጭምር ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉና ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ልጆቻቸውንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘው መምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ትርጉም »